Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጡ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ ደመቀ በማብራሪያቸው÷ የኢትዮጵያ መንግስት የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የመንግስት ልዑክ ጥቅምት 14 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ሊካሄድ በታሰበው ውይይት ላይ እንደሚገኝም ነው አቶ ደመቀ ያረጋገጡት፡፡

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅና የግዛት አንድነቷን ለማረጋገጥ በምትወስደው እርምጃ ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አይነት ጫና እንደማትቀበልም አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ተደራሽ ለማድረግ ከሁሉም አካላት ጋር ለመስራት ዝግጁ እንደሆነችም ነው የተናገሩት።

በማብራሪያው ላይ የተሳተፉ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች መንግስት ለሰላም እንዲሁም የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

አቶ ደመቀ በማብራሪያቸው አሸባሪው ህወሓት በአውደ ውጊያ እየተሸነፈ ሲመጣ የፈፀማቸው ግፎች ከተጠቀሰውም በላይ መሆኑን ጠቁመው፥ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በሽብር ቡድኑ ፕሮፖጋንዳ በመስከር በንፁሃን ዜጎች ላይ ጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸማቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአሸባሪው ህወሓት ጥቃት ሳይደርስበት በፊት ከትግራይ ህዝብ ጋር በሰላም እና በማህበራዊ ጉዳዮች በመተሳሰር ይኖር እንደነበር ያስታወሱት አቶ ደመቀ፥ ሰራዊቱ በትግራይ በነበረባቸው ጊዜያት የአካባቢውን አርሶ አደሮች ሰብል በመሰብሰብ፣ የአንበጣ ወረርሽኝን በመከላከል እገዛ ሲያደርግ ነበርም ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም በርካታ ወንጀሎችን የፈፀመው ህዋሃት እና የሽብር ቡድኑ ደጋፊዎች በሚያሰሙት የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ብዙ መስዋዕትነት የከፈለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ስም ሊጠፋ አይገባም ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል።

አንዳንድ የዲፕሎማሲ አጋር አካላት በንፁሀን ዜጎች ላይ የአየር ጥቃት ተፈፅሟል በሚል በሚያስተጋቡት የተሳሳተ መረጃ መንግስትን እንዳሳዘነውም አስረድተዋል።

ይህን የተሳሳተ መረጃም በተባበሩት መንግስታት ሳይቀር አንዳንድ ተወካዮች ሲያስተጋቡ መደመጣቸውን በመጥቀስም፥ ጉዳዩ መንግስትን እንዳሳዘነው ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ላለማሻከር እንደነዚህ አይነት መሰረተ ቢስ ክሶችን በሆደ ሰፊነት ሲመለከታቸው እንደቆየም አስርድተዋል፡፡

ስም ማጥፋቶች እና መሰረተ ቢስ ክሶችን የኢትዮጵያ መንግስት ከሚገባው በላይ እንደታገሰ ጠቅሰው ÷ መሰል አካሄዶች ሊታረሙ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ላይ የተከፈቱ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች በጊዜ ሒደት እየጠሩ እንደሚመጡም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ለሰላም ንግግር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ጥሪ መተላለፉ ብዙም እንዳላስገረማቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ ከተኩስ አቁም ጥሪው በተቃራኒ እንዳልቆመች ሁሉም እንደሚያውቁ ገልፀዋል፡፡

መንግስት በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት የተናጠል ተኩስ አቁም ጥሪ ያደረገችው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደነበር ጠቅሰው፥ በወቅቱ በድርድር ላይ የተመሰረተ ተኩስ አቁም እንድናደርግ ነው የተነገረን ሲሉም ነው ለዲፕሎማቶቹ ያብራሩት፡፡

የዚህ የተኩስ አቁም ጥሪ የተደረገው ህወሓት ሽንፈት እየገጠመው ሲሄድ እንደሆነ በማንሳት ይህን ጥሪ ያደረጉ አካላት ከህወሓት የተለዩ እንዳልሆኑ አውቃለሁ ሲሉም አክለዋል፡፡

የግጭቱን አጀማመር እና ያለበትን ሁኔታ በዝርዝር ያብራሩት አቶ ደመቀ ዲፕሎማቶቹ እውነታውን እንዲረዱ እንደሚፈልጉ ገልጸውላቸዋል፡፡

የየሀገራቱ መንግስታትም የትኛውንም አቋም ቢይዙም በእውነተኛው መሰረት ላይ እንዲሆንም ጠይቀዋል።

በምንይችል አዘዘው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.