Fana: At a Speed of Life!

የ2014 ዓ.ም ብሔራዊ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በስኬት ተጠናቋል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገራችን ዕድገት እና ብልጽግና የሚረጋገጠው የሥነ ምግባር እና የዕውቀት ጥራት ባለው የሰው ኃይል መሆኑ ይታወቃል። ፖሊሲና አሠራሯን በዚሁ ልክ ቀምራለች። ይኽ ጅምሯ በጥልቀት በተጠና የትምህርት ፍኖተ ካርታ ሥራ ተተግብሮ ታይቷል።

እጅግ አጓጊ በሆነው በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ተራምዷል። የትምህርት መሪዎች፣ መምህራንና ወላጆች በታላቅ ቅንጅት በመሥራት ላይ ናቸው። የዚህ የለውጥ ሥራ አካል የሆነው ተማሪዎችን በሐቅ እና በሳይንሳዊ መንገድ የመመዘን ሥራ ታላቅ እመርታ አሳይቷል።

የዚሁ ለውጥ አካል የሆነው የ2014 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናም የጥረቶቹ ተከታይ ሆኖ በታላቅ ስኬት ተጠናቅቋል። በቀደመው የማኅበራዊ ሳይንስ የፈተና አሰጣጥ ላይ የታዩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ተገምግመው በተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና ወቅት የተሠራው ሥራ እጅግ አመርቂ ሆኗል። የተፈጥሮ ሳይንስ የፈተና መርሃ ግብርም በመላ ሀገራችን በስኬት ተጠናቅቋል።

የፈተና አሰጣጡ ስኬት በሌሎችም ሀገር አቀፍ ምዘናዎች ሊተገበሩ የሚችሉ የተሻሉ አሠራሮችን አስተምሮ አልፏል። በሁሉም ደረጃ ያሉ ተማሪዎች በራሳቸው ሥራ ብቻ ተማምነው መቆም እንደሚኖርባቸው አስተምሯል። በትምህርትም ሆነ በሕይወት፣ በሥራም ሆነ በኃላፊነት መስኮች የአጭበርባሪነት በር እየተዘጋ የሚሄድ መሆኑን ማረጋገጫ ሰጥቷል። በአንፃሩም በመጪዋ ኢትዮጵያ በራስ ጥረት እና ላብ መተማመን ብቻ ዋጋ የሚያገኝ መሆኑን አስረግጧል።

ፈተናው ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎችን እና መምህራንን ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ፣ ለመመገብ፣ ለማሳደር፣ ጤና ለመጠበቅና ጸጥታን ለማስጠበቅ መቻሉ በሀገራችን የተገነባውን ዐቅምም ያሳያል።

ፈተናዎቹ በየሚሰጡበት አካባቢ ያለው ሕዝብ ለመፈተን የሄዱትን መምህራን በፍቅር የተቀበለበት፣ ባሕል ወጉን ያካፈለበት፣ የቱሪስት መስሕቦቹን ያስጎበኘበት መንገድ የሀገራችንን ሕዝቦች ወንድም እኅታማማችነት አጠናክሯል። በዚህ ታሪካዊ ስራ ስኬት ከዝግጅት ጀምሮ እስከፍፃሜው አስተዋፅኦ ያደረጉትን ሁሉ መንግስት ከፍ ያለ ምስጋና ያቀርባል።

ጥቅምት 11 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.