Fana: At a Speed of Life!

“ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን እቆማለሁ ድምፄንም አሰማለሁ” በሚል መሪ ቃል በመዲናዋ የተጠራው ህዝባዊ ሰልፍ ደምቆ ሰላማዊ ሆኖ መካሄዱን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)  በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአዲስ አበባ ህዝብ በዛሬው እለት ከጫፍ ጫፍ በመነሳት “ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን እቆማለሁ ድምፄንም አሰማለሁ” በሚል መሪ ቃል ደማቅ ህዝባዊ ሰልፍ ማድረጉን የከተማዋ አስተዳደር አስታውቋል።

ህዝቡ በዚህ ሰልፍ መልእክቱን እጅግ ጉልህና ግልፅ በሆነ መንገድ ለመላው አለም በማስተላለፍ፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መጠናቀቁን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።

ለዚህም መላውን የከተማዋን ነዋሪ፣ የፀጥታ ሃይል እንዲሁም ሰልፉን ያስተባበሩ የሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላትን አስተዳደሩ አመስግኗል።

 

የአስተዳደሩ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዛሬ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ!!
በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአዲስ አበባ ህዝብ በዛሬው እለት ከጫፍ ጫፍ በመነሳት ‹‹ከኢትዮጵያ ጎን እቆማለሁ ፤ ድምፄንም አሰማለሁ›› በሚል መሪ ቃል ባካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ደማቅና በሆነ መንገድ ተካሂዶ መልእክቱን እጅግ ጉልህና ግልፅ በሆነ መንገድ ለመላው አለም በማስተላለፍ፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተጠናቋል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን በእርግጥም ሰላም ወዳድ ህዝቦች ነን፡፡ ሰላም ወዳድነታችንና ለሰላም ዘብ መቆማችን በተደጋጋሚ በተግባር ያርጋገጥን ህዝቦች ነን፡፡ ነገር ግን በሉአላዊነታችንና በግዛት አንድነታችን ከመጡብን ደግሞ በአብሮነት እና በህብረት ቆመን ሃገራችንን የምንከላከል ፤ ለሃገራችን አስፈላጊውን ሁሉ መስዋእትነት የምንከፍል ፤ ኢትዮጵያን በውድ የደምና የአጥንት ዋጋ ያሸጋገርን ወደፊትም የምናሸጋገር ፅኑዕ እና ሃገር ወዳድ ህዝቦችም ጭምር ነን፡፡
ዛሬም ይህ ሀገር ወዳድነት በከተማችን መስቀል አደባባይ ተረጋግጧል፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የከተማችን ነዋሪ የሀገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል፤ በማለት ከየአቅጣጫው በመጉረፍ የፖለቲካ አመለካከት ብሄር፤ እምነት ልዩነት ሳይኖር በአንድነት እጅ ለእጅ በመያያዝ ድምፁን ከፍ አድርጎ በማሰማት ህዝባችን ሰላማዊና ሃገር ወዳድ መሆኑን ለጠላትም ለወዳጅም በማያወላዳ መልኩ ማሳየት ችሏል፡፡
የከተማችን ነዋሪዎች በነቂስ በተሳተፉበት በዚህ ፍፁም ሰላማዊ በሆነና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ጎልቶ በታየበት የሰላማዊ ሰልፍ ወጣቶች ሴቶች ጎልማሶች ፤ እናቶችና አባቶች፤ አካል ጉዳተኞች ፤መምህራን ፤ ተማሪዎች የመንግስት ሰራተኞች ፤የግል ድርጅት ሰራተኞች አርቲስቶችና ታዋቂ ሰዎች የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም አባት አርበኞች በአጠቃላይ ከሁሉም አይነት የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ የከተማችን ነዋሪዎች ገና ከሌሊት ጀምሮ በነቂስ በድቅድቅ ጨለማ ገንፍሎ በወጣ ሃገር ፍቅር ስሜት በመውጣት በየመንገዱ ድምፃቸውን እያሰሙ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መልእክታቸው አስተላልፈው ወደየመጡበት በሰላም ተመልሰዋል፡፡
ለዚህም መላውን ሰላም ወዳድና የሰላም አምድ የሆነው የከተማችንን ነዋሪ ፤የፀጥታ ሃይል እንዲሁም ይህ ሰልፉ የተሳካ እንዲሆን ያስተባበራችሁና ያቀናጃችሁ የሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት በተጨማሪም በየደረጃው የምትገኙ አመራሮች የከተማ አስተዳደራችን ስላበረከታችሁት ታላቅ አስተዋፅኦ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
አሁንም ቢሆን የጀመርነውን ሃገራችንን ከጠላት የመጠበቅ እንቅስቃሴ አጠናክረን በመቀጠል፤ ለመካላከያ ሰራዊታችንን አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋችንን እንድንቀጥል እያሳሰብን ፤ በየአካባቢው ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የውጪና የሃገር ውስጥ ጠላቶቻችን ቅጥረኞችን ከፀጥታ ሃይሉ ጋር በመተባበር በመከላከልና አጋልጠን በመስጠት ዘላቂ ሰላማችንን እናድናረጋግጥ አደራ ለማለት እንወዳለን፡፡
በመጨረሻም የጀመርነው የሃገራችንን ብልፅግና እውን የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች በማስቀጠል ዋነኛው የሉአላዊነት ምንጭ ራስን በመቻል ከጥገኝነት በመላቀቅ የሃገርን ብልፅግና ማረጋገጥ በመሆኑ እጅ ለእጅ ተያይዘን በደም ተገነባችዋን ሃገራችንን በላባችን ከፍ በማድረግ የኢትዮጵን ብሎም የከተማችንን ብልፅግና እውን እንድናደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን!!
ኢትዮጵያ በልጆቿ አብሮነትና ህብረት ታፍራና ተከብራ ትኖራለች!!
ጥቅምት 12 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.