Fana: At a Speed of Life!

በወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው አምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ዙሪያ በወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው አምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የውይይቱ ዋና ዓላማ የዘርፉን የሦስት ወራት አፈጻጸም መሠረት በማድረግ በቀጣይ ዘርፉን በምርት አቅርቦትና በገቢ መጠን ለማሳደግ፣ የዘርፉ ተዋናዮች በስራ ላይ ስለገጠሟቸው ችግሮችና መፍትሄዎች ለመወያየት ነው ፡፡

በተጨማሪም ከመንግስትና ከግል ባለሃብቱስ ምን ይጠበቃል የሚሉት ላይ ምክክር ለማድረግ ያለመ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡

በውይይቱ ላለፉት ሦስት ወራት ከወጪንግድ 86 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የውጪ ምንዛሬ መገኘቱን በቀረበው ሪፖርት ተነስቷል፡፡

የወጪ ንግድ አፈጻጸምን ለማሳደግ ውጤታማ የክትትልና ድጋፍ ስርዓቶች፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎቶችን መዘርጋት፣ አዳዲስና ነባር የህግ ማዕቀፎችን የመከለስ እና ቅንጅታዊ አሰራሮችን የማጠናከር ስራ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት የሚኒስቴሩ የወጪ ምርት ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘሪሁን አበበ ናቸው፡፡

በውይይት መድረኩ የዘርፉን ቀጣይ አፈጻጸም ለማሳደግ ሚኒስቴሩ የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ እንደተገለጸ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችም በጥራትና አቅርቦት የተሻለ ምርት በማምረት፣ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶች ላይ በመሰማራት፣ ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከርና ተወዳዳሪ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የአምራች ኢንዱስትሪ ባለሃብቶች ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ነው የተነሳው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.