Fana: At a Speed of Life!

በግብርናው መስክ የተጀመሩ የልማት ስራዎች በምግብ ራስን ከመቻል ባሻገር ለኢኮኖሚ ሉዓላዊነት መሰረት የሚጥሉ ናቸው- የመንግስት የስራ ሃላፊዎች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብርናው መስክ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች በምግብ ራስን ከመቻል ባሻገር ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በጅማ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የተለያዩ የልማት ስራዎችንና የቦንጋ ዩኒቨርሲቲን የልማት እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ ሚኒስትሮች በአካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ልማት ስራዎች እንደ ሀገር ትልቅ የሽግግር አቅም መሆናቸውን ገልጸዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ÷በተለያዩ አካባቢዎች የግብርና እና ሌሎችም የልማት ስራዎች በምግብ ራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረት የስኬት መንገድ ማሳያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በከተሞች ጭምር የግብርና ልማት በስፋት በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰው÷በብዙ መልኩ የተሳኩ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው÷በቦንጋ የታየው አስደናቂ ስራ በሌሎችም ተመሳሳይ የልማት ስራ ከተከናወነ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ስኬት የሚረጋገጥ መሆኑን ያመላከተ ነው ብለዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች እንደ ሀገር የሚታዩት የግብርና ልማት ስራዎችም አስደናቂ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ተጠሪ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ በአካባቢው ቀደም ሲል ያልተለመዱ አዳዲስ የግብርና ልማት ስራዎችን በስፋት መመልከታቸው ጠቁመው÷በዚህም የኢትዮጵያን በምግብ ራስን የመቻል እንዲሁም የእድገትና ብልጽግና ተስፋ እውን የማድረግ ትክክለኛ አቅጣጫ መሆኑ የታየበት እንደሆነ ገልጸዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ጉዳይ ሃላፊ ዛዲግ አብርሃ÷በሁሉም መስክ የተመለከትናቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያ ከዝቅተኛ አምራችነት በመሸጋገር ላይ መሆኗን የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል።

እንደ ሀገር በማክሮ ኢኮኖሚ እና በግብርና ልማት ለውጥና እመርታዎች እየታዩ እንደሆነ መግለጻቸውንም ኢዘአ ዘግቧል፡፡

ሃላፊዎቹ በግብርናው መስክ ምርታማነትን ለማስፋት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች በምግብ ራስን ከመቻል ባሻገር ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.