Fana: At a Speed of Life!

የጠላት ዓላማ ኢትዮጵያን በድህነት ማንበርከክ ቢሆንም ሊሳካለት አልቻለም – ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠላት ዓላማ ኢትዮጵያን በድህነት ማንበርከክ ቢሆንም ይህ እንደማይቻል አሁን እየታየ ያለው ሰብል ማሳያ ነው ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ ተናገሩ፡፡

በርዕሰ መስተዳድሩ የተመራ ልዑክ በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ሀጂ መሐመድ አወል እርሻ ድርጅት፣ ሶፊያ ዑመር እርሻ ልማት እና ቦረር እርሻ ልማት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በክላስተር ሆነው እያለሙት ያለውን የበቆሎ ምርጥ ዘር ሰብል ጎብኝተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ ÷ ባለሀብቶች ዘር በማልማት ስራ ላይ መሰማራታቸው ጠላትን በግንባር ገጥሞ ድል ከማድረግ ባልተናነሰ መልኩ ለሀገራቸው እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም ብለዋል።

በምርጥ ዘር አቅርቦት ዘርፍ የሚደረገውን ጥረት የክልሉ መንግስት እንደሚደግፍም ነው ያረጋገጡት።

ጠላት ኢትዮጵያን በድህነት ለማንበርከክ ይፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህ እንደማይቻል አሁን እየታየ ያለው ሰብል ማሳያ ነውም ብለዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሶፊያ ካሳ በበኩላቸው÷ ባለሀብቶች እያካሔዱት ያለው ልማት እንደ ሀገር የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም ነው ያነሱት።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ÷ ባለፉት ዓመታት የምርታማነት መቀነስ ዋነኛ ችግር የምርጥ ዘር አቅርቦት አለመመጣጠን እንደነበር ገልጸዋል፡፡

መንግስት ችግሩን ተገንዝቦ ባቀረበው አማራጭ ምርጥ ዘርን በራስ አቅም መሸፈን ትኩረት ተሰጥቷል ማለታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ባለሀብቶቹ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት÷ ዘንድሮ እየተባዛ ካለው ምርጥ ዘር ከፍተኛ የሆነ የዘር አቅርቦት እንደሚጠበቅ መግለፃቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በእርሻ ልማቱ እየተባዛ ካለው ዘር 70ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን እንደሆነም ነው የተነገረው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.