ዓለምአቀፋዊ ዜና

ኢራን 40 የጋዝ ተርባይኖች ለሩሲያ ልትሸጥ ነው

By Alemayehu Geremew

October 24, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢራን በራስ ዐቅም ያመረተቻቸውን 40 የጋዝ ተርባይኖች ለሩሲያ ለመሸጥ የኮንትራት ስምምነት መፈራረሟ ተገለጸ፡፡

አሁን ላይ ኢራን 85 በመቶ የሚሆነውን ከጋዝ አቅርቦት ጋር የተያያዙ መሳሪያዎች እና ቁሶች በሀገር ውስጥ የማምረት ዐቅም እንዳላት ይነገራል።

ምንም እንኳን አሜሪካ በኢራን ላይ ጠንካራ ነው ያለችውን ማዕቀብ ብትጥልም ኢራን ግን የጋዝ ምርቷን በእጥፍ ማሳደግ እንደቻለች ነው የኢራን ጋዝ ኢንጂነሪንግ እና ልማት ኩባንያ ኃላፊ ሬዛ ኖሻዲ የተናገሩት።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢራን እና ሩሲያ ትብብራቸውን በተለያዩ መስኮች እያሳደጉ መምጣታቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

በፈረንጆቹ ሐምሌ ወር ላይ ሩሲያ በኢራን የነዳጅ ኢንዱስትሪ ላይ መዋዕለ-ነዋይ ለማፍሰስ እስከ 40 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ የመግባቢያ ሥምምነት መፈራረማቸውን ሺንዋ “ሻና” የተሰኘውን የኢራን የነዳጅ ሚኒስቴር የዜና ምንጭ ጠቅሶ ዘግቧል፡፡