Fana: At a Speed of Life!

መንግሥት የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅና የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው – አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 15 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላማዊ ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ እና የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት “ሰላም እና ደህንነት በአፍሪካ” በሚል አጀንዳ ላይ ትናንት ዝግ ስብሰባ አካሂዷል።

አምባሳደር ታዬ ስብሰባውን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ በሰሜን ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህ ወቅትም መንግሥት የሁሉንም ኢትዮጵያውያን መብቶች ለማክበርና ለማስከበር፣ የሰላማዊ ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ እንዲሁም የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትና ስርጭትን ለማሳለጥ የተወሰዱ ተጨባጭ እርምጃዎችን በተመለከተም ማብራሪ ሰጥተዋል።

በትግራይ የሚገኙ ስትራቴጂክ ቦታዎችና ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የመቆጣጠር ሕጋዊነትና ተጨባጭ ምክንያትን በተመለከተም ማስረዳታቸውን ጠቅሰዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጉዳይ በመርህ ላይ የተመሰረተ አተያይን እንደሚጠይቅም በዚህ ወቅት ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያ መንግሥትና የጸጥታ ኃይሎች ትግራይን ጨምሮ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል መንቀሳቀስ እንደሚችሉም ነው ለምክር ቤቱ ያስረዱት።

በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑንም ነው አምባሳደር ታዬ በማብራሪያቸው የገለጹት።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የምክር ቤቱ አባላት ለሂደቱ ስኬት ድጋፍ እንዲያደርጉና በሂደቱ ላይ ጥርጣሬን የሚያጭሩ አቋሞችን ከማንጸባረቅ እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.