የሸቀጦች ዋጋን ለማረጋጋት ውስጣዊ አቅሞችን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገሪቱ የሸቀጦች ዋጋን ለማረጋጋት ውስጣዊ አቅሞችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች፥ በሀገር ውስጥ አጭር በሚባሉ ጊዜያት ተገንብተዉ ወደ ስራ እንደሚገቡ ፕሮጀክቶች ሁሉ ምጣኔ ሃብቱ ላይ ተመሳሳይ ጠንካራ ስራ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
የዘርፉ ተመራማሪ ዶክተር ደግየ ጎሹ፥ ብሄራዊ ባንክ በቅርቡ ያሳለፈው መሰረታዊ ሸቀጦች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡበት አሰራር አላማውን እንዳይሰት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል ፡፡
የቁጥጥርና ፊስካል ዲሲፕሊን ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ነው የመከሩት፡፡
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገር ውስጥ ያለውን የምጣኔ ሃብት ችግሮች ተገንዝበዉ የውጭ ገንዘባቸውን ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲልኩ መስራት እንደሚገባም ነው ምክረ ሃሳባቸውን የሰጡት፡፡
አለም አቀፍ ተጽእኖዎች እንደተጠበቁ ሆነው የሸቀጦችን ዋጋ ለማረጋጋት በሃገር ውስጥ ያሉ አቅሞችን ሁሉ አሟጦ መጠቀም እንደሚገባም ነው የተገለፀው፡፡
ሌላኛዉ የዘርፉ መምህርና ተመራማሪ መሃመድ ኢሳ፥ ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦችን በሀገር ውስጥ የመተካቱ ስራ በቂ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አንስተዋል ፡፡
የሚተገበሩ ስራዎችን ለውጥ በየጊዜዉ መመዘን እና ለተግባራዊነቱ መተባበር እንደሚገባም ጠቁመዋል ፡፡
ሌሎች መስኮችን በማነቃቃት የውጭ ምንዛሬ ምንጮችን ማስፋት እንደሚገባም ባለሙያዎቹ ተናግረዋል ፡፡
በአወል አበራ