Fana: At a Speed of Life!

ከ449 በላይ ለሚሆኑ የወባ ተጋላጭ ወረዳዎች አጎበር ማሰራጨት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ449 በላይ ለሚሆኑ የወባ ተጋላጭ ወረዳዎች የወባ በሽታ መከላከያ ምትክ አጎበር ማሰራጨት መጀመሩን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የጤና ሚኒስቴር፣ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ እና የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የወባ ሣምንት በአማራ ክልል ባሕርዳር ዙሪያ ወረዳ አንዳሳ ቀበሌ ተከብሯል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንደገለጹት÷ ሀገሪቱ በጤናው ዘርፍ ካሳካቻቸው የሚሊኒየም ግቦች መካከል በወባ መቆጣጠር፣ መከላከል እና ማጥፋት ዙሪያ የተከናወኑ ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡

ይሁን እንጅ “ወባ ጠፍቷል” በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ እና አጎበርን በአግባቡ ባለመጠቀም፣ ያቆሩ ውሀዎችን የማስወገድ እና የኬሚካል እርጭት ሥራዎች ላይ መዘናጋት በመኖሩ የወባ በሽታ ማንሰራራት ጀምሯል ብለዋል፡፡

በዚህም ለወባ በሽታ የበለጠ ተጋላጭ ለሆኑ በ449 ወረዳዎች ስር ለሚገኙ 6 ሺህ 134 ቀበሌዎች 19 ነጥብ 7 ሚሊየን ምትክ አጎበር የማከፋፈል ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ወራት ተጨማሪ አጎበር ማሰራጨት፣ የኬሚካል እርጭትና ውሀማ ቦታዎችን የማፋሰስ እንዲሁም የቅኝት ሥራዎች ህብረተሰቡን እና አጋሮችን በማሳተፍ ይከናወናል መባሉን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የተጨማሪ አጎበሮች ግዥ ተፈጽሞ የማጓጓዝ ሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመው÷ ሁሉም መዋቅሮች ወባን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና ዜሮ ደረጃ ለማድረስ የታቀደው ግብ እንዲሳካ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.