ከ8ኛ ክፍል ተፈታኞች ገንዘብ በመሰብሰብ የፈተና መልስ ሰጥተዋል የተባሉ 6 መምህራን ተከሰሱ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ተፈታኞች ገንዘብ በመሰብሰብ የፈተና መልስ ሰጥተዋል የተባሉ ርዕሰ መምህሩን ጨምሮ አምስት ሰዎች ላይ ክስ ተመሰረተ፡፡
ክስ የተመሰረተው አንደኛ ርዕሰ መምህር አብዱ ሸኩር ጀማል፣ ሁለተኛ ተከሳሽ የድሬዳዋ ፖሊስ ዋና ሳጅን አብዲ ዩያ ፣ ሶስተኛ መምህር መሃመድ ጠሃ አብዱላሂ እና አራተኛ መምህር ማሙሽ አካሉ ተክሌ፣ እንዲሁም አምስተኛ መምህር ሲሳይ ደስታ ሚጆና ላይ ነው ተብሏል፡፡
ከሰኔ 28 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በሚሰጥበት ወቅት አንደኛ ተከሳሽ በድሬዳዋ አስተዳደር በቢዮአዋሌ ክላስተር የለገቢራ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር እንደነበሩም ነው የተጠቀሰው፡፡
ርዕሰ መምህሩ ለፈተናው ሂደት ደህንነትና ጥበቃ በት/ቤቱ ከተመደበው የድሬዳዋ ፖሊስ አባል ከሆነው 2ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር የት/ቤቱ ተፈታኝ የነበሩ 57 ተማሪዎችን ገንዘብ በመሰብሰብ “የፈተና መልስ ተሰርቶ እንዲሰጣችሁና ለፈታኞች መስተንግዶ የሚሆን እያንዳንዳንዳችሁ ተማሪዎች 100 ብር አዋጡ” ማለታቸውም ነው የተነገረው፡፡
̎ያልከፈለ አይፈተንም” በማለትም ገንዘቡን ለአንድ ተማሪ እንዲሰጡ በማድረግ ከ44 ተማሪዎች ከእያንዳንዳቸው 100 ብር፣ ከ11 ተማሪዎች ከእያንዳንዳቸው 50 ብር አጠቃላይ 4 ሺህ 950 ብር ተሰብስቦ ለ2ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ጥቅም ላይ እንደዋለ ተገልጿል፡፡
ለተማሪዎቹ የባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ፣ የህብረተሰብ ሳይንስ እና የስነ-ዜጋ የትምህርት ዓይነቶችን ፈተና መልስ በማለት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች እየዞሩ ተማሪዎቹ እንዲሞሉ አድርገዋልም ነው የተባለው፡፡
ውጤት ይፋ ሲደረግ ሁሉም ተማሪዎች ከማለፊያ ነጥብ በታች ማምጣታቸውንም ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ተከሳሾች በፈፀሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል በአጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡
ክሱ ለተከሳሾች የደረሳቸው ሲሆን÷ የድሬዳዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ተከሳሾች ከጠበቃ ጋር ተማክረዉ ለመቅረብ በጠየቁት መሰረት ለጥቅምት 22 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!