በአፋር ክልል በተወሰኑ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ መስመር መልሶ ግንባታ ሥራ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አገልግሎት ተቋርጦባቸው የቆዩ የአፋር ክልል ወረዳዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የኤሌክትሪክ መስመር የጥገና፣ የመልሶ ግንባታ እና የአዲስ መስመር ዝርጋታ ሥራ መጠናቀቁን የአፋር ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ፡፡
በጥገናው 52 ነጥብ 36 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ መስመር፣ 120 ነጥብ 35 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመር እና 21 ትራንስፎርመሮች የመትከል ሥራ ተከናውኗል፡፡
በአሸባሪው ህወሓት በተዘረፈው ተንቀሳቃሽ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ምክንያት አገልግሎቱ ተቋርጦባቸው የነበሩት ጭፍራ፣ እዋ፣ ከልዋን እና አውራ ወረዳዎች እየተገነባ የሚገኘው ተለዋጭ የማከፋፈያ ጣቢያ ሲጠናቀቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኛሉ መባሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡
በሌላ በኩል አብኣላ፣ በራህሌ፣ ኮነባ፣ ኢረብቲ እና መጋሌ ወረዳዎችን ዳግም ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ለማድረግ የጉዳቱ መጠን ለማጥናትና ወደ ጥገና ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብሏል፡፡