Fana: At a Speed of Life!

አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ አሸባሪው ህወሓትን በማዳን ስራ ላይ ተጠምደዋል – ላውረንስ ፍሪማን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የምዕራቡ ዓለም አንዳንድ ሀገራት ኢትዮጵያ የተረጋጋች እንዳትሆን አሸባሪው ህወሓትን በማዳን ስራ ላይ መጠመዳቸውን አሜሪካዊው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ተናገሩ።

ኢትዮጵያ በምትከተለው ስኬታማ ፖሊሲና ባላት የመልማት እምቅ አቅም የተነሳ ከአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራትና ድርጅቶች ተደጋጋሚ ጫናዎች እየደረሰባት መሆኑን ገልጸዋል።

አሜሪካዊው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ፥ የተወሰኑ ምዕራባውያን አፍሪካን በቁጥጥራቸው ስር አድርገው እንደፈለጉ የማዘዝ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው።

በአህጉሪቱ ጠንካራ መንግስትና ሀገር እንዳይኖር እየሰሩ ስለመሆኑ በመጠቆምም፥ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት በማባባስ ደካማ ሀገር የመፍጠር እቅድ ይዘው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በቅርቡ መንግስት የሀገር ሉዓላዊነትን ለማጽናት በትግራይ ክልል ቁልፍ ከተሞችን እየተቆጣጣረ ሲመጣ ምዕራባውያኑ በመንግስት ኃላፊዎቻቸው፣ በተቋማትና በመገናኛ ብዙሃኖቻቸው ጭምር ጫና እያሳደሩ ያሉትም ለዚሁ ነው ይላሉ።

በእነዚሁ አካላት በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ጫና ለእነሱ የሚላላክ መንግስት ለመፍጠር ካላቸው የረጅም ጊዜ እቅድ የሚቀዳ ስለመሆኑም ተንታኙ ገልጸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሓኖም የተጣለባቸውን ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ለአሸባሪው ህወሓት ድጋፍ ሲያደርጉ ምዕራባውያኑ በዝምታ የሚያልፉት ከጀርባ ካላቸው ድብቅ ፍላጎት የተነሳ መሆኑንም ነው ያነሱት።

ከዚህ ባለፈም አንዳንድ ምዕራባውያን የሰሜኑን ጦርነት በፍርደ ገምድል ውሳኔያቸው የሽብር ቡድኑ በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ ግፍ የተፈጸመባቸውን ሚሊየን ዜጎች መዘንጋታቸው አሳዛኝ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራትና ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች መጀመሪያ ለሀገሪቱ አዲስ አስተዳደር ሲያደርጉት የነበረው ድጋፍ ቢቀጥል ኖሮ አሁን በኢትዮጵያ የተከሰቱት ችግሮች ሁሉ አይፈጠሩም ነበር ብለዋል።

በመሆኑም መንግስት የእነዚሁ አካላትን የረጅም ዓመታት ሴራ በአግባቡ መገንዘብና አንድነትን በማጠናከር የአሸባሪውን ህወሓት ጉዳይ በማንኛውም አማራጭ ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት አለበት ነው ያሉት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.