Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በምርት ዘመኑ ከ143 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በምርት ዘመኑ ከ143 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ ተገለጸ።

በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ የተመራ የልዑካን ቡድን በምስራቅ ጎጃም ዞን በሸበል በረንታ ወረዳ በክላስተር የለማ የጤፍ ማሳን ጎብኝቷል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት እንደተገለጸው በምርት ዘመኑ በክልሉ 4 ነጥብ 85 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል የተሸፈነ ሲሆን፥ ከዚህም 143 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በምርት ዘመኑ ዝናብ በወቅቱ አለመዝነብና የግብዓት እጥረት ስጋት ፈጥሮ እንደነበር አንስተው ፥ ተፈጥሯዊም ሰው ሰራሽ ችግሮቹን በመሻገር ካለፉት ዓመታት የተሻለ ምርት ለማምረት የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ሃይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው፥ የአፈር ማዳበሪያ እጥረትን ለመቅረፍ 50 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በምርት ዘመኑ ምርታማነትን በ27 በመቶ ፤ ምርትን ደግሞ በ20 በመቶ መጨመር የሚያስችል ስራ መሠራቱንም ነው ያስረዱት።

በበጋ መስኖ 250 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ሃይለማርያም ፥ በዚህም 10 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚመረትና 5 ሚሊየን ኩንታል ለውጭ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን ገልጸዋል።

በላይነህ ዘለዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.