Fana: At a Speed of Life!

የቻይና አምራች ኩባንያዎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና ባለሀብቶችና አምራች ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እና ያሉ አምራቾችም ኢንቨስትመንቶቻቸውን እንዲያስፋፉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጥሪ አቀረበ፡፡

ኮርፖሬሽኑ በቻይና ከኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ ከኤምባሲው የሚሲዮን መሪ እንዲሁም ከፋይናንስና የኢኮኖሚ ሀላፊዎች ጋር በኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ የበይነ መረብ ውይይት አካሂዷል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞንን ጨምሮ የዘርፉ የሥራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች በበይነ መረብ ውይይቱ ተሳትፈዋል።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በዚሁ ወቅት÷ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ ኮርፖሬሽኑ እያከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀዋል።

የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን በበኩላቸው÷ የቻይና አምራች ኩባንያዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እያከናወኑ ያሉት ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት በመታገዷ ዘርፈ ብዙ ጫናዎች ቢኖሩም ያሉ አምራች ኩባንያዎች ሌሎች የገበያ አማራጮችን በመፈለግ ምርቶቻቸውን እንዲያስፋፉ ተቋሙ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣና ከቻይና አምራች ኩባንያዎች ጋርም በቅርበትና በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በቀጣይም ዘርፉ ከሚመለከታቸው ሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት መሰል መድረኮች በቀጣይ ተዘጋጅተው ውይይት እንዲካሄድ ከስምምነት ተደርሷል መባሉን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ገንብቶ በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከ22 በላይ የቻይና አምራች ኩባንያዎች እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.