ኃላፊነት የጎደላቸው አካላት ለአደገኛ የፖለቲካ አጀንዳ ሲባል እየፈጠሯቸው የሚገኙ መሠረተ ቢስ ውንጀላዎችን ኢትዮጵያ ታወግዛለች – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
በምዕራባውያን የተለያዩ አካላት አማካኝነት በኢትዮጵያ ላይ የሚነዙ የሐሰት ስም ማጥፋቶችን የኢትዮጵያ መንግሥት ፈጽሞ አይታገሥም።
እነዚህ አካላት ኢትዮጵያ ውስጥ የከፉ ወንጀሎች ሊፈጸሙ ይችላሉ በሚል የሕወሓትን ጊዜ ያለፈበት ፕሮፓጋንዳ እንደ በቀቀን መድገማቸው አሳፋሪ ነው።
እነዚህ አካላት የሚከሱት ፍንጮችን ወይም ተጨባጭ ክስተቶችን መሠረት አድርገው አይደለም፤ የመፈጸም ዕድል አለ በሚል ያልተጨበጠ ግምት እንጂ።
እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ የተሻለ ስም ያላቸው ተቋማት ሳይቀሩ ይሄንን በኢትዮጵያ ላይ ተቀነባብሮ የሚለቀቅ ፕሮፓጋንዳ ለመቃወም አለመቻላቸው ነው።
ጥቂቶቹም ስለ ኢትዮጵያ የተነገረውን ስም ማጥፋት በማመን ሳይሞኙ እንዳልቀሩ ይገመታል። አንዳንዶችም እነዚህን የሐሰት ክሶች ኢትዮጽያን ለማንበርከክ ሊጠቀሙባቸው ይፈልጋሉ።
ይሄን መሰል አስደንጋጭ ክሶችን አቅርቦ የኢትዮጵያ መንግሥትን በማስጨነቅ በሕወሓት ላይ እየወሰደ ያለውን የመከላከል እርምጃ ለማስቀየስ የሚችሉ መስሏቸው ከሆነ ተሳስተዋል።
አንዳንዶችም የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ይህንን ቡድን ለማዳን እየተረባረቡ ነው። አንዳንድ ምዕራባውያን ባለ ሥልጣናት ጭምር ይሄንን የሐሰት ክስ የሚነዙት ኢትዮጵያ ትእዛዛቸውን አልቀበል ስላለቻቸው መሆኑን በይፋ መናገር ጀምረዋል።
ይህ ጊዜ አመጣሽ የሐሰት ክስ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ጨርሶ አይቀይረውም።
እነዚህ ጉምቱ ተቋማትና ወሳኝ ተዋንያን፣ በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው በዚህ የሃሰት ዘመቻ እየተሳተፉ ይገኛሉ። ይሄን የመሰሉ የከፉና ሊወገዙ የሚገባቸው ውንጀላዎች ለፖለቲካ ዓላማ መዋላቸው ኃላፊነት የጎደለውና አሳፋሪ ነው።
ይህን ለመሰለው አደገኛ ስም ማጥፋት ምላሽ ሳይሰጡ ታግሦ ማለፍ የሚቻል ባለመሆኑ በከፋ መልኩ በኢትዮጵያ ላይ ያልተረጋገጡና ፖለቲካዊ ዓላማ ያላቸውን ውንጀላዎች ከሚያቀርቡ ከአንዳንድ ሀገራትና ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት የኢትዮጵያ መንግሥት መልሶ እንዲያጤን ተገዷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከመነሻውም በግልፅ እንዳስታወቀው በአፍሪካ ኅብረት በኩል እየተደረገ ላለው የሰላም ንግግር ቁርጠኛ ነው።
ምክንያቱም ግጭቱን በሰላማዊና ቋሚ በሆነ መንገድ ለመፍታት የጸና አቋም አለውና። በሌላም በኩል በግጭቱ ምክንያት የተከሠቱ የሰብአዊ መብትና የሰብአዊነት ጥሰቶችን ተጠያቂ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ለመግለፅ ይወዳል፡፡
ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት