ከንቲባ አዳነች በአሜሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲ ሲ ዲ ኤም ቪ እና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያዩ፡፡
ከንቲባዋ በዋሺንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመገኘት ነው በኢንቨስትመንት እና ቢዝነስ የስራ መስኮች ላይ ከተሰማሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር የተወያዩት፡፡
በውይይቱ የዳያስፖራ አባላቱ አዲስ አበባ በብራዚል ሪዮ ዲጄኔሪዮ የ2022 ሚላን ፓክት አዋርድ እና በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ በተካሄደው የሲ 40 የዓለም ከተሞች በማሸነፏ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።
ከንቲባ አዳነች እስካሁን የተገኙ ድሎችም ሆኑ ፈተናዎችን ለመሻገር በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሚና ወደር የለሽ እንደሆነም አንስተዋል።
አሁንም አዲስ አበባን ከዲፕሎማቲክ ማዕከልነቷ ባሻገር ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነችና እንደ ስሟ አበባ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በኢንቨስትመንት፣ በመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ በንግድ ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በእውቀት ሽግግር፣ የከተማዋን የጤና ቱሪዝም ማዕከልነት እቅድ በማሳካት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የዳያስፖራ አባላቱም በሀገራቸው እየተካሄደ ባለው አጠቃላይ እንቅስቃሴና እየመጣ ባለው ለውጥ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው የከንቲባዋን ጥሪ መቀበላቸውና በሀገር ጉዳይ በንቃት መሳተፍ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።
ሆኖም ወደ ሀገር ሲመጡ የሚያጋጥማቸውን የቢሮክራሲ ችግሮች መንግስት እንዲቀርፍላቸው መጠየቃቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከንቲባ አዳነችም ይህንን ችግር ለመፍታት ስርዓት መገንባት እና ማጠናከር እንዳለበት ገልፀው ይህንን ማድረግ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አመላክተዋል፡፡