17 የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ጥምረት በሰላም ንግግሩ ውጤት ላይ ያልተገባ ጫና የሚፈጥሩ አካላትን ተቃወሙ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመላው ዓለም የሚገኙ 17 የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ጥምረት አባላት በሰላም ንግግሩ ውጤት ላይ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላትን ተግባር ተቃውመዋል፡፡
የጥምረቱ አባላት ባወጡት መግለጫ መንግስት በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለውን ተግባር እንደሚደግፉ ገልጸው÷ የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ያለውን የሰላም ንግግር ጨምሮ እያከናወናቸው ባሉ ተግባራት ላይ አንዳንድ ሀገራት የሚፈጥሩትን ያልተገባ ጫና እንቃወማለን ብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ግጭትና ውድመት አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መምጣቱን አስታውሰዋል።
መንግስት ለሰላም ካለው ጽኑ ፍላጎት በመነሳት ከፍተኛ ውድመት ያስከተለውን ይህን ግጭት ከቀሰቀሰው አካል ጋር ያለቅድመ ሁኔታ በመነጋገር ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት በተደጋጋሚ ፍላጎት ማሳየቱን ነው የገለጹት፡፡
በኢትዮጵያም ሆነ በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን የውይይት ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ በሰላም ንግግር ላይ በመሳተፍ ላይ ላለው የኢትዮጵያ መንግስትና ይህን ላመቻቹ አካላት አባላቱ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
የሰላም ንግግሩን ተገን አድርጎ በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና በመፍጠር በመስዋዕትነት የተገኘውን ድል ለመንጠቅ የሚደረገውን እቅስቃሴ እንደሚቃወሙም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሰላም ንግግሩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ እና አሸባሪ ቡድኑ እንደገና እንዲደራጅና ለሌላ ጥፋት ዕድል እንዲያገኝ የሚያደርጉ ማናቸውንም ምክረ ሀሳቦች እንደማይደግፉም ነው ያስታወቁት።
አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረትና ሌሎችም አካላት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የሰላም ንግግሩን ውጤት ለመቀየር የሚደረጉ ማናቸውንም አይነት ጫናዎች እንደሚቃወሙ በመጥቀስም፥ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ከግጭት ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት በሚችሉት ሁሉ ለመደገፍ ሁልጊዜም ዝግጁ ነን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡