Fana: At a Speed of Life!

የግብርና ኢንዱስትሪዎች ለሀገር ብልፅግና የላቀ ድርሻ እንዳላቸው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለአልሚ ባለሀብቶች ማስተዋወቅ መርሐ ግብር በሐዋሳ ተካሄደ፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በልማት የጠነከረች ሀገር በመፍጠር ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ብለዋል፡፡

ጥንት አባቶቻችን በህይወትና በደም ያስተላለፉልንን ሀገር እኛ በልማት በመድገም ለየትኛውም ጫና የማትንበረከክ ሀገር መፍጠር አለብንም ነው ያሉት።

ለዚህ ደግሞ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች የሚያለሙ ባለሀብቶች ትልቅ ሀላፊነት እንዳለባቸው አንስተዋል።

ኢትዮጵያን ከድህነት አረንቋ ለማውጣት መንግስት በልዩ ትኩረት የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማስፋፋት 29 ቢሊየን ብር መድቦ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክን ለማስፋፋትና አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት 6 ነጥብ 65 ቢሊየን ብር ወጪ በማድረግ ግንባታው መጀናወኑን አስረድተዋል።

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ፀጋ በለፀገች ሀገር በመሆኗ ይህንን ሀብት በማልማት በእድገት ማማ ላይ ማቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

እድገትን ለማፋጠንና ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት ባለሀብቶች በአምራች ኢንዱስትሪ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በክልሉ ውስጥ ያልተነኩ የግብርና ግብዓቶች መኖራቸውን በመጥቀስም ለአልሚ ባለሀብቶች የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

በቢቂላ ቱፋ እና ታመነ አረጋ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.