Fana: At a Speed of Life!

ከ195 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን ከጥቅምት 11 ቀን እስከ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል ከ195 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዙን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ 143 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 52 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸውን ነው የገለጸው፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በብርበራና በጥቆማ የተያዙ ሲሆን የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 11 ግለሰቦች እና 36 ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተነግሯል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ እና ሞያሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መሆናቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.