በ500 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ ለሚገነባው የቶጎ ጫሌ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት መሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ በ500 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ ለሚገነባው የቶጎ ጫሌ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የመሰረተ ድንጋይ አስቀመጡ፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ እንዲሁም ከሶማሌ ክልል ውሃ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀሰን መሀመድ ጋር በመሆን ነው የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት፡፡
ፕሮጀክቱ በ500 ሚሊየን ብር ወጪ የሚገነባ ሲሆን÷ የቶጎ ጫሌ ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር የሚቀርፍና ከ60 ሺህ በላይ ዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ታምኖበታል፡፡
የፕሮጀክቱ ወጪም ሙሉ በሙሉ በፌደራል መንግስት በተለይም በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንደሚሸፈን ተገልጿል፡፡
ፕሮጀክቱን በአንድ አመት ከግማሽ ለማጠናቀቅ መታቀዱን የሶማሌ ክልል ውሃ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀሰን መሀመድ ሁሴን ተናግረዋል።
የቶጎ ጫሌ ከተማ ህዝብ ለበርካታ አመታት ሲያነሳው የነበው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ማግኘቱንና ክልሉም የህብረተሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስ እየሰራ ነው መባሉን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡