Fana: At a Speed of Life!

በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን ወደላቀ ውጤት ለማሸጋገር እየተሠራ ነው- አቶ አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን ወደላቀ ውጤት ለማሸጋገር እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

የክልሉ የ2015 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል፡፡

በጸጥታ ችግር ምክንያት ወደግብርና ሥራ ሳይገቡ የቆዩ አካባቢዎች በዘንድሮው የ2014/15 የምርት ዘመን ወደሥራ መግባታቸውን ተከትሎ እስካሁን 842 ሺህ 141 ሔክታር በዘር መሸፈኑ ተገልጿል፡፡

አቶ አሻድሊ ሀሰን በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ግብርናውን በሜካናይዜሽን ለመደገፍ በክልሉ የተጀመረውን ለአርሶአደሩ የእርሻ ትራክተር የማቅረብ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የስንዴ ምርት ለሀገራችን ዘርፈብዙ ፋይዳ ያለው በመሆኑ በክልሉ ስንዴን ለማምረት በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የማዕድንና የኢንቨስትመንት ዘርፉን የበለጠ ሪፎርም በማድረግ የክልሉን ኢኮኖሚ እንዲደግፍ የሚያደርጉ አሠራሮችን መተግበር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

የወርቅ ምርት ሙሉ በሙሉ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዳይገባ የሚያደርጉ ሕገወጦችን ስርዓት ማስያዝ ቀዳሚ ትኩረት ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ጠቁመው÷ የክልሉን ዘላቂ ሰላም ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ወደ ሰላም የተመለሱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋምና ወደልማት ማስገባት እንደሚገባም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ፣ የመንገድ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ የክልሉ መንግስት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.