የሀገር ውስጥ ዜና

አየር መንገዱ ወደ ዚምባቡዌ ቡላዋዮ ከተማ በረራ ጀመረ

By Tamrat Bishaw

October 30, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዙምባቡዌ ሁለተኛ ግዙፍ ወደሆነችው ቡላዋዮ ከተማ በረራ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

አየር መንገዱ ከሐረሬ እና ቪክቶሪያ ፎልስ በተጨማሪ ወደ ቡላዋዮ በረራ መጀመሩ የሀገራቱን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡

ቡላዋዮ በኢንዱስትሪ ማዕከልነቷ እና በቱሪስት መዳረሻነቷ የታወቀች ከመሆኗ በተጨማሪ÷ ለደቡብ አፍሪካ ድንበር ከተማ በመሆኗ እና ለቦትስዋና እንዲሁም ዛምቢያ ቅርብ ስለሆነች ለተጓዦች የተመረጠች ናት።

የቡላዋዮን ጨምሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳረሻውን ወደ 63 ከፍ አድርጓል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሣምንት ለሦስት ቀናት ወደ ዙሪክ የሚያደርገውን የቀጥታ በረራ ጀምሯል።

የዙሪኩን ጨምሮ አየር መንገዱ ወደ አውሮፓ ሀገራት የሚያደርገውን የበረራ ቁጥር ወደ 19 ከፍ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት÷ በረራው የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ያጠናክረዋል፡፡

የቀጥታ በረራው ኢትዮጵያ ከስዊዘርላንድ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት እንደሚያሳድገውም ተናግረዋል፡፡

በኃይለየሱስ መኮንን እና ትዕግስት ብርሃኔ