Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋ የሚዘክር ሰልፍ በዋሽንግተን ዲሲ ሊካሔድ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ ሁለተኛ ዓመት የሚዘከርበትና የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ የፊታችን ሐሙስ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
ሰልፉ መነሻውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መድረሻውን ደግሞ “ካፒቶል ሂ” በማድረግ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚከናወን ነው የተገለጸው፡፡
በሰልፉ ላይ አሸባሪው ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ እንደሚዘከር የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዋሺንግተን ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ ጣሰው መላከሕይወት ለኢዜአ ገልጸዋል።
ሰልፈኞቹ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚያደርጉትን ጫናና ጣልቃ ገብነት የሚቃወሙና አሜሪካ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን እንድትቆም የሚጠይቁ መፈክሮችን ያሰማሉ ብለዋል።
በሰልፉ ላይ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ይሳተፉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም ሕዳር 3 ቀን 2015 ዓ.ም በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች “ለአገራዊ ጥሪ ወገናዊ ምላሽ” በሚል መሪ ሀሳብ የገቢ ማሰባሳቢያ መርሐ-ግብር በዋሺንግተን ዲሲ እንደሚካሄድ ነው አቶ ጣሰው የገለጹት።
ሰልፉን ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር ዲሲ ግብረ ኃይል በአሜሪካ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት፣ከተለያዩ ተቋማትና አገር ወዳጆች ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀውም ታውቋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.