Fana: At a Speed of Life!

በባህር ዳር ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የሴተኛ አዳሪዎች ፕሮጀክት የብዙዎችን ህይወት እየታደገ መሆኑ ተመለከተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት እየተከናወነ የሚገኘው የሴተኛ አዳሪዎችን ህይወት የሚቀይር ፕሮጀክት የብዙዎችን ህይወት እየታደገ መሆኑን በባህርዳር ከተማ ህይወታቸውን በሴተኛ አዳሪነት ሲመሩ የነበሩ ሴቶች ገለጹ፡፡

ከፕሮጀክቱ ጋር በተያያዘ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው በዚሁ አካባቢ ህይወታቸውን በሴተኛ አዳሪነት የሚመሩ ሴቶች እንዳሉት፥ የተደረገላቸው ድጋፍና ክትትል አጠቃላይ ፕሮጀክቱ እስካሁን ያልተሞከረ እና ህይወት የሚቀይር ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በሌሎች አካባቢዎች አገልግሎት እንዲሰጥ እና ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል ።

ፕሮጀክቱ በዚሁ ስራ በሚተዳደሩ ሴቶች ላይ አካላዊና አዕምሯዊ ለውጥ በማምጣት ከዚህ አስከፊ ህይወት እንዲወጡ የምክር እና የተሃድሶ ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን፥ በኢኮኖሚ ራሳቸዉን እንዲችሉም የማቋቋሚያ ድጋፍ ይደረጋል ነው የተባለው።

እስካሁን በስድስት ዙር ስልጠና ከ200 በላይ ሴተኛ አዳሪዎች በወንዶችና በሴቶች የጸጉር ሙያ፣ በምግብ ዝግጅትእና በልብስ ስፊት ተመርቀዉ ወደ ስራ በመግባት ራሳቸዉን እየለወጡ ይገኛሉ፡፡

የፕሮጀክቱ አላማም በሴተኛ አዳሪነት የተሰማሩ ሴቶችን መልሶ ማቋቋምና በአስተማማኝ፣ ምርታማነት እና ማህበራዊ ተቀባይነት ባለው የኑሮ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዲሳተፉ ማስቻል ነዉተብሏል፡፡

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ፕሮጀክቱን እያስፈጸመ የሚገኘዉ በእየሩሳሌም ህጻናት እና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት በኩል ሲሆን፥ የገንዘብ ድጋፍን ያገኘዉ ከስዊድን አለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ሲዳ) በኢትዮጵያ የስዊድን ኢምባሲ በኩል መሆኑ ተገልጿል፡፡

በፍሬህይወት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.