Fana: At a Speed of Life!

በሰሜን እዝ ላይ የተፈፀመው ጥቃት መታሰቢያ ጥቅምት 24 ቀን በመላ ኢትዮጵያ ይካሄዳል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “መቼም አንረሳውም” በሚል መሪ ቃል በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመው ጥቃት ሁለተኛ ዓመት መታሰቢያ የፊታችን ጥቅምት 24 ቀን በመላ ሀገሪቱ  እንደሚካሄድ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ እለቱን በተመለከተ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የትግራይ ክልልን ሲጠብቁ የነበሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት በአሸባሪው ህወሓት ጭካኔ በተሞላበት ድርጊት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም መጨፍጨፋቸውን አስታውሰዋል።

ዕለቱም በመላው ሀገሪቷ እንደሚዘከር ጠቅሰው÷ተግባሩ መቼውንም ቢሆን የማይረሳ የሀገር ክህደት ወንጀል ሆኖ በታሪካችን ሲነሳ የሚኖር ይሆናልም ብለዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት በጦርነቱ ወቅት የህይወት መስዋዕትነት በሰላሙ ጊዜ ደግሞ ከትግራይ ማህበረሰብ ጋር እርሻን የሚያርስና ትምህርት ቤት የሚገነባ፣ መንገድ እየሰራ እና የህክምና አገልግሎት እየሰጠ የትግራይ ህዝብ ጠባቂ ሆኖ ሲያገለግል የኖረው ጀግናው ሰራዊት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በከሃዲዎች በጭካኔ የተጨፈጨፈበት እለት ነው ብለዋል፡፡

የሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መጠቃት ኢትዮጵያን የማፍረስ እኩይ ተግባር ጅማሮና ታስቦ የተደረገ ተልዕኮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሁሉም የመንግስት ተቋማት በፌደራል እና በክልል በየእርከኑ ያሉ ተቋማት እለቱን እንደሚያስቡት ጠቅሰዋል፡፡

የፊታችን ጥቅምት 24 ቀን “መቼም አንረሳውም” በሚል መሪ ቃል እለቱ ሲዘከርም ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት የከፈለውን መስዕዋትነት እውቅናና ክብር ለመስጠት እና ጥቃቱ ጥቁር የታሪካችን አካል መሆኑን በማስገንዘብ በሀገራችን እንዳይደገም የማስገንዘብ አላማዎችን ይዟል ነው ያሉት።

እለቱ በመላው ሀገሪቱ ሲዘከር በጥቅምት 24 ከቀኑ አራት ሰዓት ሁሉም ቀኝ እጁን በደረቱ ላይ በማኖር በመሪ ቃሉን በማለትና አሽከሪካዎችም ለአንድ ደቂቃ ክላክስ በማሰማት ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፋቸውን ያሰማሉ ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም ለመከላከያ ሰራዊቱ ከሚደረጉ የገንዘብና የአይነት ድጋፎች ባለፈ በተዘጋጀው የአጭር የፅሁፍ መልእክት ቁጥር 6800 ላይ ዜጎች የሚችሉትን የገንዘብ መጠን በማበርከት ድጋፍ ያደርጋሉም ነው የተባለው።

በፀጋዬ ወንደሰን እና የሻምበል ምሕረት

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.