የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጀማሪ የፈጠራ ባለቤቶችን ለመደገፍ 4 ቢሊየን ብር መድቤያለሁ አለ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጀማሪ የፈጠራ ባለቤቶችን ለመደገፍ 4 ቢሊየን ብር መመደቡን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሃንስ አያሌው እንደገለጹት÷ ባንኩ የፈጠራ ባለቤቶችን ለመደገፍ 4 ቢሊየን ብር የመደበ ሲሆን የባንኩን ድጋፍ የሚሹ ስራ ፈጣሪዎች በስፋት ከመጡ በጀቱን ከዚህም በላይ ከፍ ያደርጋል፡፡
እስካሁን ባለው በግብርናው ዘርፍ የመጡ የፈጠራ ሃሳቦች የአዋጭነት ጥናት አጥንተው የቢዝነስ እቅድ እንዲያቀርቡ እንደተነገራቸውም ነው የገለጹት።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የግል ዘርፉ በዲጂታል ኢኮኖሚው መሳተፍ የሚያስችል ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሆነም አስረድተዋል።
ባንኩ ስራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ አዲስ ሃሳብ ይዞ የሚመጣ ስራ ፈጣሪ ፈጠራው የራሱ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ የፈጠራ ሃሳቡ አዋጭ መሆኑን በማጥናት ወጪውን ሸፍኖ ሃሳቡ ወደስራ እንዲቀየር ድጋፍ እንደሚደረግም ነው የገለጹት፡፡
ስራ ፈጣሪ ወጣቶች በበኩላቸው ÷የፋይናንስ ተቋማት ለሀገር የሚጠቅሙ አዳዲስ የፈጠራ ሀሳቦችን እውን ለማድረግ በቂ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
እንደ ሀገር ጀማሪ የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች ከሚገጥሟቸው ችግሮች አንዱና ዋነኛው የገንዘብ እጥረት መሆኑን ያነሳሉ።
የሀገርና የማህበረሰብ ችግሮችን መነሻ በማድረግ መፍትሔ ይዘው የሚመጡ የፈጠራ ሀሳቦች ሀገርን ስለሚጠቅሙ በቂ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።