ከአላማጣ እስከ ቆቦ ያሉ አካባቢዎች ዳግም የኤሌክትሪክ ኃይል አገኙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በከፈተው ጦርነት በደረሰ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ውድመት ኃይል ተቋርጦባቸው የነበሩት አላማጣ፣ ኮረም፣ ዋጃ፣ ጥሙጋ እና ቆቦ ከተሞች ዳግም የኤሌክትሪክ ኃይል አግኝተዋል፡፡
አገልግሎቱ እንደገና ለመመለስ በተደረገ ፈጣን የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ጥገና እነዚህ አካባቢዎች ዳግም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘታቸውን የወልዲያ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ወልደሰማያት ገልፀዋል፡፡
አካባቢዎች ከአላማጣ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ የሚያገኙ በመሆናቸው ለረጅም ጊዜ ኃይል ተቋርጦቦቸው መቆየቱንም ጠቅሰዋል፡፡
ሆኖም በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ የመከከለኛና የዝቅተኛ መስመር የኤሌክትሪክ መስመሮችን እንደገና በመጠገን አገልግሎቱ መመለስ እንደተቻለ መናገራቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም የዲስትሪክቱ ሰራተኛች ባደረጉት እልህ አስጨራሽ የጥገና ስራ ከአላማጣ – ቆቦ ድረስ የወደሙ የመካከለኛ ኤሌክትሪክ መስመሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠገናቸውን አስታውስዋል፡፡
የዲስትሪክቱ የቴክኒክ ሠራተኞች ከአላማጣ – ላሊበላ የተዘረጋውን የ66 ኬ.ቪ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ በአካባቢው ያሉ ከተሞችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡