Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚመለከታቸው ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ጥሪ አቀረቡ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመ ልዩ አጣሪ ቋሚ ኮሚቴ የመተከል ግጭት መፍትሄና ምክረ-ሀሰብ ጥናት ቡድን ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይቷል፡፡

አቶ አሻድሊ ሀሰን በዚሁ ወቅት÷በክልሉ በግጭት ምክንያት የመሰረተ ልማት፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና እና የውሃ ተቋማት ውድመት በመከሰቱ መልሶ የመገንባት ስራ ላይ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

ተፈናቃዮች ወደመደበኛ የኑሮ ደረጃ እስኪመለሱ ድረስ የሰብዓዊ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡

ክልሉ እና የሌሎች ክልሎች የፀጥታ ኃይሎች ከሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም ከህዝቡ ጋር ተቀናጅተው በመስራታቸው በመተከል ዞን አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ጠቅሰዋል፡፡

የህግ-የበላይነትን ለማስከበር በግጭቱ እጃቸው አለበት ተብሎ የተጠረጠሩ አመራሮች ሳይቀር በሕግ ጥላ ስር ሆነው ጉዳያቸው እንዲጣራ የማድረግ ስራ እየተሰራ  መሆኑንም አቶ አሻድሊ ገልጸዋል፡፡

በግጭቱ ሳቢያ ወደጫካ የገቡ፣ ወደከተማ እና ምቹ አካባቢዎች የሸሹ እንዲሁም ወደ አጎራባች ክልል የተፈናቀሉ ወገኖች መኖራቸውን መግለጻቸውንም  ከክልሉ ብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

አሁን ላይ  የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀደመ መኖሪያ  ቀያቸው የመመለስ  ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.