Fana: At a Speed of Life!

በባሕላዊ ሥራዎቿ የሥራ ዕድል ፈጣሪዋ የኪነ ኅንጻ ባለሙያ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኪነ ኅንጻ ባለሙያዋ አራራት ታምራት በኢትዮጵያ ባሕላዊ የስንደዶ ሥፌት እና የክር ጥልፍ ሥራዎች ለኢትጵያውያን ሴቶች ሥራ መፍጠር የቻለች ሴት በሚል “ላዮነሲስ ኦፍ አፍሪካ” በሣምንቱ ዕትሙ የፊት ገጹ ላይ ይዟት ወጥቷል፡፡

“ላዮነሲስ ኦፍ አፍሪካ” በሜላኒ ሀውኬን በደቡብ አፍሪካ የተመሠረተ ጀማሪ የአፍሪካ ሴት ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ ኮርፖሬሽን ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኪነ ህንጻ ሙያ የተመረቀችውን አራራት ታምራት “ምርጥ ሴት ሥራ ፈጣሪ” በሚል አሞካሽቷታል፡፡

አራራት ታምራት በኢትዮጵያ የ“ቱባ ባይ አራራት” የንግድ ምልክት ባለቤትና የሥራ ፈጠራው መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንደሆነችም ዘግቧል፡፡

የኪነ ህንጻ ባለሙያዋ ሥራ ፈጣሪ የዓመቱ ምርጥ ሥራ ፈጣሪ የሚለውን ዕውቅናም እንዳገኘች አትቷል፡፡

ሥራ ፈጣሪዋ ወጣት የኢትዮጵያ ሴቶች ባላቸው ሙያ እና ጥበብ ግድግዳዎች ላይ የሚሰቀሉ እና ወለል ላይ ለአበባ ማስቀመጫነት የሚያገለግሉ በሥንደዶ የተሠሩ ሥፌቶችን እና የአበባ ማስቀመጫዎችን ፣ በጨርቅ ላይ የተጠለፉ የትራስ እና የአልጋ ልብሶችን በማምረት ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ እያገዘች መሆኗንም ጠቅሷል፡፡

አራራት ታምራት አሁን ላይ ለ39 ሰዎች ሥራ እንደፈጠረች እና 35 ያህሉ ሴቶች መሆናቸውንም ነው “ላዮነሲስ ኦፍ አፍሪካ” ሥራ ፈጣሪዋን ዋቢ አድርጎ የዘገበው፡፡

ሥራ ፈጣሪዋ ወጣት እስከ ፈረንጆቹ 2030 እስከ 500 ለሚደርሱ ሴቶች ሥራ የመፍጠር ራዕይ እንዳላትም ኮርፖሬሽኑ በመረጃው አመላክቷል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከሥራ ፈጣሪዋ ጋር በነበረው ቆይታ የምትሠራቸው ሥራዎች በኪነ ህንጻ ሙያ የተደገፉ የቴክኖሎጂ ንድፎችን በመጠቀም እንደምትሠራ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በዓለማየሁ ገረመው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.