በበጋ መስኖ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዷል – የግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጋ መስኖ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት መታቀዱን የግብርና ሚኒስቴሩ አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የእርሻና ሆርቲካልቸር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን በሰጡት መግለጫ ÷በመስኖ ስንዴ ከሚለማው መሬትም ከ52 ሚሊየን ኩንታል ምርት በላይ ይጠበቃል ብለዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት የስንዴ ምርት ወደ ውጭ ለመላክ ያዘችውን እቅድ የሚያሳካ እንደሚሆን አንስተዋል፡፡
ወደ ውጭ ከሚላከው ምርት በተጨማሪ የሀገር ውስጥ የስንዴ ፍጆታ በባለሙያዎች መጠናቱንም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡
ለሀገር ውስጥ ፍጆታ 97 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር መለስ ÷ በመኸር እና በመስኖ የለማው የስንዴ ምርት የሀገር ውስጥ ፍጆታን ከመሸፈን አልፎ ኤክስፖርት ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።
የሰብል ስብሰባው በተጀመረው የ 2014/15 የመኸር ምርት ዘመን አጠቃላይ ከሚጠበቀው 400 ሚሊየን ኩንታል ምርት ውስጥ 108 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ም ጠቁመዋል።
የመኸር ሰብል በመሰብሰብ ሂደት የምርት ብክነት እንዳይከሰት 1 ሺህ 500 የሰብል መሰብሰቢያ ኮምባይነሮች እንደሚሰማሩ አስገንዝበዋል፡፡
በዙፋን ካሳሁን እና ሜሮን ሙሉጌታ