የሀገር ውስጥ ዜና

በአህጉሪቱ የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ትስስር በመፍጠር የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማጎልበት እንደሚገባ ተገለጸ

By Amele Demsew

November 01, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ አህጉር የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ትስስር በመፍጠር የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማጎልበት እንደሚገባ  የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ፡፡

ሰሞኑን በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ የቀድሞ መሪዎች በፓን አፍሪካኒዝም ላይ ልምዳቸውን አካፍለዋል።

በጉባዔው ላይ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ባደረጉት ንግግር÷ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደት እንዲኖር በዓለምአቀፍ ደረጃ ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

ግጭትን በማስወገድ የመሰረተ ልማት ትስስርን ማጠናከር እና በልማት መስኮች እድሎች መፍጠር እንሚገባም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የወጣቶችን አቅም መጠቀም እና የአመራር ሚናቸውን ማጎልበት ይገባል ማለታውን የውጭ ጉይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የጋና የቀድሞው ፕሬዚዳንት ድራማኒ ማሀማ በበኩላቸው÷ የአፍሪካ ባህላዊ እሴቶችን በማዳበር የራሳችን ሞራል እና ማንነት መጠበቅ ይገባል ብለዋል፡፡

በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ ሐሳቦች አፍሪካዊ ማንነታችን እያሳጡን ነው ያሉት ድራማኒ ማሀማ÷ ይህንን በመከላከል እና አፍሪካዊ እሴቶችን በመጠበቅ ረገድ ወጣቶች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡