በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት መታሰቢያ የፊታችን ሐሙስ በኦሮሚያ እና ጋምቤላ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት “መቼም አንረሳውም” በሚል መሪ ሐሳብ በኦሮሚያ እና በጋምቤላ ክልሎች ጥቅምት 24 ቀን 2015ዓ.ም ታስቦ ይውላል።
ይህንን አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ባወጣው መግለጫ÷ የጀግኖቻችንን ሕይወት እና የከፈሉትን መስዋዕትነት እያሰብን ለሀገራችን ነፃነት በአንድነት ዘብ እንቆማለን ብሏል፡፡
ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ቢፈልጉም ኢትዮጵያ ግን በልጆቿ ደም ተከብራ፣ በዜጎቿ ላብ ተጠናክራ ትቀጥላለች ሲል ገልጿል፡፡
የጀግኖቻችንን ሕይወት እና የከፈሉትን መስዋዕትነት እያሰብን ለሀገራችን ነፃነት በአንድነት እንቆማለንም ነው ያለው።
ዕለቱ የሚታሰበው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጀግንነትና መስዋዕትነት ምልክት ተደርጎ መወሰድ ስላለበት መሆኑን የገለጸው ደግሞ የጋምቤላ መንግስት ኮሙኒኬሽን መግለጫ ነው።
መግለጫው በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ዘግናኙ ድርጊት የተፈፀመበት ቀን ኢትዮጵያ የተፈተነችበት፣ በልጆቿ ላይ አሰቃቂ ድርጊት የተፈፀመበት ጨለማ ቀን ሆኖ እንደሚታሰብ አመላክቷል፡፡
የጋምቤላ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽኅፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግ እንዳሉት ÷ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሽብር ቡድኑ ህወሓት የተፈፀመበትን ጥቃት በሀገር እና በወገን የተፈፀመ ክህደት ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።
ዕለቱ አሁንም ድረስ ለዘለቀውና መንግስት እና ህዝብ ተገዶ ለገባበት የሀገርን ህልውና የማፅናት ትግል ሰበብ በመሆኑን አንስተው ዕለቱ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደሚታወስም ተናግረዋል።