ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለአፍሪካ አንድነትና ፓን አፍሪካኒዝም አስተዋጽኦ ላደረጉ የአፍሪካ ሀገራት የቀድሞ መሪ ቤተሰቦች ሽልማት አበረከቱ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 22 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን ጨምሮ ለአፍሪካ አንድነትና ፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ ላደረጉ 17 የአፍሪካ ሀገራት የቀድሞ መሪ ቤተሰቦች ሽልማት አበረከቱ።
የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ጉባኤ ማጠቃለያ መርሐ-ግብር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄዷል።
በማጠቃለያ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለአፍሪካ አንድነትና ፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ ላበረከቱ 17 የአፍሪካ ሀገራት የቀድሞ መሪ ቤተሰቦች ሽልማት አበርክተዋል።
ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ የዛምቢያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኬኔት ካውንዳ፣ የቀድሞ የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ፣ የዚምባቡዌ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ የሞሮኮ የቀድሞ ንጉስ ሀሰን ሁለተኛ፣ የጊኒ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አህመድ ሴኩ ቱሬ፣ የማሊ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ማዲቦ ኬይታ፣ የኮትዲቯር የቀድሞ ፕሬዚዳንት ፍሊክስ ሆፌት ቦይኚ እና የሴኔጋል የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሊኦፖልድ ሴዳር ሴንጎር እውቅና ካገኙት መካከል ይገኙበታል።
በአካል ሽልማቱን መቀበል ያልቻሉ ቤተሰቦች በአፍሪካ ሕብረትና ዲፕሎማሲያዊ አማራጮች እንደሚያገኙም ተገልጿል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁት የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ጉባኤ ከጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ሲካሄድ ቆይቷል።
የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤና ፍልስፍና ለአዲሱ የአፍሪካ ትውልድ ማስተዋወቅና አብሮነትን ማጠናከር ዓላማው ባደረገው በዚህ ጉባኤ ከ42 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ወጣት መሪዎችና የአፍሪካ ሀገራት የቀድሞ መሪዎች ተሳትፈዋል።
በጉባኤው የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች ልምዳቸውን እንዳካፈሉ ኢዜአ በዘገባው አስታውሷል።