አዲስ አበባ በዳታ ማዕከል ግንባታ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ አቅም ከዓለም 2ኛ ደረጃን ይዛለች
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 23 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አባበ ከተማ በዳታ ማዕከል ግንባታ ዘርፍ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ አቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከቤጂንግ ቀጥላ 2ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ጥናት አመላክቷል፡፡
“ኤፍ ዲ አይ ኢንተለጀንስ” በቅርቡ ባካሄደው ጥናት፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዳታ ማዕከል ግንባታ ዘርፍ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ተመራጭ የሆኑ ከተሞችን ዝርዘር ይፋ አድርጓል፡፡
ጥናቱ ከፈረንጆቹ ጥር 2003 እስከ ሰኔ 2022 ድረስ በዳታ ማዕከል ግንባተ ዘርፍ ጥሩ የሚባል የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን የሳቡ 100 ከተሞችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ጥራት ያለው እና ዘመናዊ የዳታ ማዕከል ግንባታ፣ የተሟላ መሰረተ ልማት ዝርጋት፣ በቂ የግንባታ ቦታ ማዘጋጀት፣ የሰው ሃይል እና ሌሎች መመዘኛ መስፈርቶች በጥናቱ ተካተዋል።
በዚህ መሰረት የአፍሪካዋ መዲና አዲስ አበባ ከለንደን፣ ሻንጋይ፣ ቶኪዮ፣ ኢስታንቡል እና ሴኡል ቀድማ፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዳታ ማዕከላት ግንባታ ዘርፍ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ሁለተኛ ደረጃ መያዟን ጥናቱ አመላክቷል፡፡
የቻይናዋ ቤጂንግ ደግሞ በዚህ ዘርፍ የዓለማችን ቀዳሚዋ ከተማ ሆናለች ነው የተባለው።
በመቀጠል አዲስ አበባ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራቱን የጠበቀ የዳታ ማዕከል በተመጣጣኝ ዋጋ ለመገንባት በበርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ተመራጭ እየሆነች መምጣቷም ነው የተጠቀሰው።
ለአብነትም የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ኩባንያዎች በቴሌኮም ዘርፍ እንዲሰማሩ መፍቀዱን ተከትሎ ሳፋሪኮም የተሰኘው ኩባንያ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አንስቷል፡፡
ኩባንያው በአዲስ አበባ ከተማ በ100 ሚሊየን ዶላር ወጪ የመጀመሪያ የሆነውን የዳታ ማዕከል ለመገንባት ማቀዱም ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ ባለፈም የጂቡቲው ዊንጉ አፍሪካ፣ የአሜሪካው ራክሲዮ እንዲሁም የካምቦዲያው ሬድ ፎክስ ኩባንያዎች በአዲስ አበባ በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ማቀዳቸውን ጥናቱ አመላክቷል።
የእንግሊዟ መዲና ለንደን ደግሞ ከአዲስ አበባ በመቀጠል በዳታ ማዕከል ግንባታ ዘርፍ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨትመንትን በመሳብ ተመራጭ ከተማ መሆኗ ተገልጿል፡፡