Fana: At a Speed of Life!

በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት መታሰቢያ በነገው ዕለት በመዲናዋ በተለያዩ ሁነቶች ይዘከራል

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 23 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት መታሰቢያ መርሐ ግብር በነገው ዕለት በተለያዩ ሁነቶች እንደሚዘከር የአዲስ አበባ የከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
 
አስተዳደሩ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ አባላት አሸባሪው ህወሓት በክህደት ጥቃት መፈጸሙ ሁልጊዜም የሚታወስና ፈፅሞ የማይዘነጋ ዕለት መሆኑን አንስቷል፡፡
 
የሀገርን ሉዓላዊነትን ለማስከበር ሐሩር እና ቁሩ ሳይበግራቸው በቀበሮ ጉድጓድ የቆዩት የሰሜን ዕዝ አባላት በአሸባሪው ህወሓት ክህደት አረመኔያዊ ጭፍጨፋ የተፈፀመባቸውን ጀግኖች ሰማዕቶቻችንን ትውልድም ሲዘክራቸው ይኖራልም ነው ያለው።
 
ዛሬም በሀገር ወዳድ ልጆችዋ ሉዓላዊነቷ መከበሩን ሰንደቋ ከፍ ብሎ መውለብለቡን ቀጥሏል ያለው አስተዳደሩ ÷ ሰራዊቱ በደሙ ያጸናትን ሀገር ሌት ተቀን ሰርተን ድህነትን ተፋልመን በማሸነፍ የሀገራችንን ነጻትና ሉዓላዊነት እናጸናለን ብሏል፡፡
 
የከተማዋ ነዋሪዎችም በውጪ ጠላቶች አዝማችነት ሀገር ለመበተን ጥቃት የፈጸሙብንን ህወሓትንና ጀሌዎቹን በጀግንነት በመመከት የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ወደር የለሽ መስዋዕትነት እየከፈለ ካለው የመከላከያ ሰራዊታች ጎን እንዲቆሙ ጥሪ ቀርቧል፡፡፡
 
በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት መታሰቢያም በነገው ዕለት በመዲናዋ በሁሉም የመንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ነዋሪዎች ዘንድ በተመሳሳይ ሁኔታ በተለያዩ ሁነቶች እንደሚዘከር ተመላክቷል፡፡
 
በዚህ መሰረትም፡-
 
ከጠዋቱ 4 ሰዓት ጀምሮ ሁሉም ተሽከርካሪዎች ለአንድ ደቂቃ ክላክስ ያሰማሉ፤ ከጠዋቱ 4:30 በተመሳሳይ ሰዓት ሁሉም በከተማዋ የሚገኙ የመንግስትና የግል ተቋማት አመራሮች ፣ ሰራተኞች እና ነዋሪዎች በተሰማሩበት እና ባሉበ ቦታ በመቆም የቀኝ እጃቸውን በግራ ደረታቸው ላይ በማድረግ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው”ስለኢትዮጵያ የከፈላችሁትን አንረሳም” በማለት ለሰማዕታቱ ያላቸውን ክብር ይገልጻሉ ተብሏል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.