የሁመራ – ወልቃይት – ሽረ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እየተጠገነ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሁመራ – ወልቃይት – ሽረ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እየተጠገነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና የማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ ሀብታሙ ውቤ እንደገለፁት÷ በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡
በዚህም የሁመራ – ወልቃይት- ሽረ ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና የማከፋፈያ ጣቢያ የፍተሻ እና የጥገና ሥራ እየተከናወነ ነው መባሉን የኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመላክታል፡፡
ከሁመራ እስከ ሽረ ባለው ባለ 230 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በተደረገ የፍተሻና ጥገና ሥራ÷ 67 ቦታዎች ላይ የኮንዳክተር እንዲሁም 3 ቦታዎች ላይ የፋይበር ኦፕቲክስ መቆራረጥ አጋጥሟል ብለዋል፡፡
የሁመራ እና ወልቃይት ከተሞችና አካባቢያቸው ለረጅም ጊዜ ኃይል ተቋርጦ የቆየ በመሆኑ በአጭር ጊዜ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያኙ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡