Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ አፍሪካው የሰላም ውይይት ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አግኝቷል- ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደቡብ አፍሪካ ላይ በነበረው የሰላም ውይይት ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ማግኘቱን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በአርባ ምንጭ ከተማ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ጦርነት የሰውን ህይወት ይቀጥፋል፣ እጅ እግር ያሳጥራል፣ ንብረት ያወድማል ጥላቻንም ያበዛል ነው ያሉት።

ጦርነት እንኳን እርስ በርስ በወንድማማች መካከል ቀርቶ በማንኛውም ሀገር መካከል ቢሆን የሚወደድ፣ የሚናፈቅና የሚፈለግ ነገር እንዳልሆነም አስረድተዋል።

እኛ ሰላምን የምንወድና የምንሻ ህዝቦች እጅግ በምንወዳት ገነት በሆነችው በአርባ ምንጭ የፍቅር ከተማ ውስጥ የሰማነው ዜና ሁልጊዜ የማይረሳ በመሆኑ ጋሞዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

የጋሞ፣ የጎፋ፣ የወላይታ የጉራጌና የስልጤ፣ የሃድያ እንዲሁም የከምባታና የዚህ አካባቢ ህዝቦች በሙሉ ኢትዮጵያ ስትደፈር የኢትዮጵያ ልጆች በግፍ ሲገደሉ፥ በፈቃድ እና በደስታ በልጆቻችሁ ደምና ህይወት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማጽናት ትልቅ ዋጋ ስለከፈላችሁ ሁሉም አመራሮች እናመሰግናችኋለን ለማለት መጥተናልም ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

የአርባ ምንጭ ነዋሪ እንደ ጉራጌ ህዝብ ሰላም ወዳድ፣ ስራ ወዳድ፣ አርቆ አሳቢና በኢትዮጵያዊነቱ ጽኑ አቋም እንዳለውም አንስተዋል።

እኛ ምንፈልገው ሰላምና ብልጽግና ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ÷ በደቡብ አፍሪካ በነበረው የሰላም ውይይት ጀግኖች የጋሞ ልጆች፣ ጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች በመሬት ላይ ያስገኙትን ታሪካዊ ድል ዳግም የሚያስረግጥ የሰላም ድል ማግኘት መቻሉንም አስገንዝበዋል።

በየሻምበል ምሕረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.