Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እና ኢትዮጵያ እፎይ እንድትል ዜጎች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያውያን ሰላማችን ወደ ኋላ እንዳይመለስ፣ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እና ኢትዮጵያ እፎይ እንድትል የበኩላችሁን እንድታደርጉ አደራ እላለሁ ሲሉ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአርባምንጭ ከተማ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያውያን ከእኛ ጋር በመሆን ሰላማችን ወደ ኋላ እንዳይመለስ፣ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እና ኢትዮጵያ እፎይ እንድትል የበኩላችሁን እንድታደርጉ አደራ እላለሁ ብለዋል።

ለትግራይ ህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ትግራይ ሃገራችን፤ የትግራይ ህዝብ ደግሞ ህዝባችን ነው ስንል ቆይተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ብዙ ያልተገባ ደም መፍሰሱንና መቆሳሳል በእያንዳንዱ ላይ መድረሱን አስረድተዋል።

ጦርነት፣ ጉዳትና ኢትዮጵያን አጋልጦ የመስጠት ሂደት በመሆኑ በዚህ ይብቃ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

መከፈል የማይገባው ነገር ተከፍሏል፤ብዙ ደም ፈሷል፤ንብረት ወድሟል፤ ኢትዮጵያን ትንሹም ትልቁም ሚዲያ አሳንሰዋታል ይህም ይብቃ ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

ከሰላም ንግግር በኋላ ሸፍጦች ይበዛሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ “የተከበርከው የትግራይ ህዝብ እኛ ልባችንን ከፍተን ሰላምን ለማምጣት ዝግጁ ነን፤ ይህንን የገባነውን ቃል ለመጠበቅ ከሌሎች ወንድሞች እና እህቶች ጋር በመሆን የበኩልህን እንድትወጣ አደራ እላለሁ” ብለዋል፡፡

ተንኮል፣ ክፋት፣ ሸፍጥ እዚህ ላይ እንዲያበቃ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ጥቂቶች እየሸረቡ ኢትዮጵያን ጦርነት ውስጥ እንዳስገቡ የትግራይ ህዝብም ኢትዮጵያዊ ሚናውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

“ኢትዮጵያውያን ገንዘብ ፣የጦር መሳሪያ ብናቀብል ይገዳደላሉ ብላቹ የተጋቹ የቅርብም የሩቅም ሃገራት ኢትዮጵያ የማትፈርስ የአፍሪካ ፈርጥ ናት፤ እኛ ኢትዮጵያውን እያለን ኢትዮጵያን ማሳነስ አይቻልም፤ አይታሰብምም ብለዋል፡፡

በአንፃሩ ደግሞ በጭንቅ ጊዜ እንደ አንድ የኢትዮጵያ ክልል ከኢትዮያ ጎን የቆማችሁ ያላችሁንም ያካፈላችሁ ሃገራት ኢትዮጵያ አትረሳም ብድራታችሁን ትከፍላለች ሲሉም ተናግረዋል፡፡

“የኢትዮጵያ ኩራትና የኢትዮጵያዊነት ምልክት የሆነው የመከላከያ ሰራዊት በእናንተ መቁሰል ኢትዮጵያ ዳግም ቆማ በክብር መናገር ስለቻለች ለእናንተ ያለንን ታላቅ ክብር እንገልፃለን፤ ክብር ይገባችኋል” ነው ያሉት በመልዕክታቸው፡፡

“የብልፅግና ፓርቲ ወይም ህጋዊው መንግስት ብቻዬን ኢትዮጵያን ካልገዛሁ የሚል አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በጀመርነው አካታች ምክክርና ውይይት ሁላችንም እንሳተፍ፤ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ሃሳብ እናምጣ” ብለዋል፡፡

ህዝቡን በማወያየትም ዳግም መሰዳደብ የሌለባት ኢትዮጵያን እንድንገነባ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.