Fana: At a Speed of Life!

የደም ግፊት መንስኤ እና ምልክቶች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደም ግፊት ህመም ማለት በደም ስራችን ውስጥ ያለው ግፊት በሚለካበት ወቅት ከ140/90 በላይ ሲሆን ነው፡፡

ማንኛውም እድሜያቸው 30 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ለደም ግፊት የመጋለጥ እድል ሊኖራቸው እንደሚችል ይነገራል ፡፡

ሆኖም ከእድሜ መጨመር ጋር ተያይዞ፣ ከፍተኛ የሆነ ክብደት መጨመር፣ ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል መጠጦችን አብዝቶ መጠጣት፣ ጭንቀትና ውጥረት ውስጥ መግባት እንዲሁም በቤተሰብ ወይም በዘር የሚተላለፍ የደም ግፊት ሲኖር ተጋላጭነትን ሊጨምር ይችላል፡፡

የደም ግፊት በአብዛኛው ጊዜ የልብና የደም ስርዓትን የሚያውክ ሲሆን÷ ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች ዋና ዋናዎቹ የልብ ህመም፣ የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ፣ የኩላሊት ህመም፣ የዓይን ህመምና የማስታወስ ችሎታ ማጣት ናቸው፡፡

የደም ግፊት ዋና ዋና ምልክቶች ራስ ምታት፣ ትንፋሽ ማጠር፣ ነስር፣ የድካም ስሜት፣ የደረት ህመም፣ የእይታ መድከም፣ በሽንት ውስጥ ደም መታየት መሆናቸውን የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

እድሜያቸው 30 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎች የደም ግፊት ቅድመ ምርመራ ማድረግ ወይም የደም ግፊታቸውን መለካት እንዳለባቸው ይመከራል፡፡

በተጨማሪም ጤናማ የአመጋገብ ስርዓት መከተል፣ አካላዊ እንቅስቃሴ አዘውትሮ ማድረግ፣ ሲጋራ አለማጨስ፣ አልኮል መጠጥን አብዝቶ አለመጠጣት፣ ጭንቀትና ውጥረትን መቀነስ መከላከያ መንገዶች መሆናቸውን ከጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ገፅ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

የደም ግፊትን በመለካት፣ የደም ግፊት ህመም እንዳለብን ወይም እንደሌለብን ማወቅ እንደሚገባም የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.