የዓለም የትምህርት ትብብር ተቋም ዋና መስሪያ ቤትን በአዲስ አበባ ለመክፈት ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም የትምህርት ትብብር ድርጅት ዋና መስሪያ ቤትን በአዲስ አበባ ለመክፈት የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል፡፡
ስምምነቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ እና የዓለም ዓቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት ዋና ጸሐፊ መንሱር ቢን ሙሳላም ፈርመውታል፡፡
አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ÷መንግስት በትምህርት ልማት የሚያደረገውን ጥረት እና ከዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር የሚደርገውን ትብብር ለማሳደግ የድርጅቱ መስሪያ ቤት በአዲስ አበባ መከፈት ትብብሩን ያሳድገዋል ብለዋል።
የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ መንሱር ቢን ሙሳላም በበኩላቸው÷በማህበራዊ ፖሊሲዎች፣ይዘት እና በስርዓተ ትምህርት ውስጥ አዲስነት ለመፍጠር ድርጅቱ በኢትዮጵያ ዋና መስሪያ ቤቱን መክፈቱ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
ስምምነቱ በትምህርት እድገት ተደራሽነት እና ጥራት ለሚደረገው ጥረት እንደሚያግዝ መገለጹንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡