የኢትዮ-ሳዑዲ አረቢያ ቢዝነስ ፎረም ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ ቢዝነስ ፎረም በበይነ መረብ ተካሂዷል።
በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ የኤዥያ እና ፓስፊክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ዶ/ር ገበየሁ ጋንጋ ፥ የኢትዮጵያና የሳውዲ አረቢያ መንግስት በልማት ትብብር፣ ንግድ እና ኢኮኖሚ ልማት ዘርፎች ገንቢ የሆነ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ዛሬ የተካሄደው ፎረምም የኢትዮ-ሳዑዲ አረቢያን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶችን ስትራቴጂካዊ አጋሮችን በማጎልበት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገር ያግዛል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው ፥ ባለፉት ዓመታት መንግስት የወሰዳቸው የለውጥ አጀንዳዎችና ለግል ኢንቨስተሮች ክፍት ያልነበሩት አሁን ክፍት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኮሚሽነሯ ፥ ግብርና፣ ማዕድን ማውጣት፣ ቱሪዝምና አይሲቲ መንግስት ትኩርት የሰጣቸው የኢንቨስትመንት መስኮች መሆናቸውንም ነው ያነሱት።
የሳኡዲ አረቢያ የኢንቨስትመንት ም/ሚኒስትር ባዳር አልባዳር ፥ የሀገራቸው ባለሃብቶች ሊሰሩባቸው የሚፈልጉትን አማራጮችና ባለሃብቶች ማወቅ የሚፈልጉትን ጉዳዮች አንስተዋል።
ከማዕድን ሚኒስቴር የተወከሉት ዶ/ር ጉቱ በበኩላቸው ፥ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲደረጉባቸው አቅጣጫ ከተሰጣቸው አንዱ የማዕድን ገበያ አንዱ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።
አምባሳደር ዶ/ር ገበየሁ ፥ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በኢንቨስትመንት ዘርፍ አሁን ካለው ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የሰኡዲ አረቢያ መንግስት አምባሳደር ዶ/ር ፋሃድ ኡቤይዱላህ አልሁመይዳኒ እና ሌሎች ኃላፊዎች መገኘታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።