Fana: At a Speed of Life!

ሰላም በመገኘቱ የሚከስር ሕዝብ የለም – ዶ/ር አብረሃም በላይ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰላም በመገኘቱ የሚከስር ሕዝብም ሆነ የሕዝብ አጀንዳ የለም ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ አብረሃም በላይ ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ ሰላም በመገኘቱ የሚከስር ሕዝብም ሆነ የሕዝብ አጀንዳ የለም፤ በሕዝብ ስም የሚነግድና ጦርነትና ግጭትን የሚቸረችር ኃይል እንጂ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፋት ሁለት ዓመታት በጦርነት ጥፋትና ውድመት ስትደማ የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ ግንባር ፈጥረው ሲያስጨንቋት መክረማቸውንም አስታውሰዋል፡፡

በታሪኳ ተአምር ሊባል በሚችል ሁኔታ በ2010 ዓ.ም ሰላማዊ የኃይል ሽግግር ማድረጓን ጠቅሰው÷ አለመታደል ሆኖ ሰላማዊ ሽግግሯ ደፍርሶ እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ቆይታለች ነው ያሉት።

መላው ኢትዮጵያውያን በተለይም የትግራይ ህዝብ፣ በውጭ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት፣ ምሁራን፣ አባቶች፣ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የማህበረስብ አንቂዎች÷ ባለፋት አስቸጋሪ ጊዜያት ያለፍንበትን መከራ ለመቀልበስ ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችንን፣ የህግና የፍትህ ችግሮቻችንን፣ ህገ-መንግስታዊ ጥያቄዎችን፣ ክስና ውንጀላዎቻችንን ጨምሮ ትርክቶቻችንን የምናስተካክልበት፣ የሰከነ የውይይትና የምክክር አውድ እንዲፈጠር ፍንጣቂውን የሰላም ጮራ የምንከባከብበት ጊዜ መሆኑን ልብ ልንል ይገባናል ብለዋል፡፡

የተፈተነውን አንድነታችንን ለማጎልበት ፍጹም ታጋሽነትንና ሆደ ሰፊነትን ብንላበስም ሁላችንም የምናሸንፍበት ጊዜ ሩቅ አይሆንምም ነው ያሉት።

ከሩቅ ሆናችሁ ህዝባችን የሚፈልገውን ሰላም ለማጨለም ሌላ ተጨማሪ መከራ ለማስቀጠል የምትንቀሳቀሱ ግለሰቦች እና ቡድኖች ካለፈው ለመማር አለመፈለጋችሁን እና የጭካኔያችሁን ጥግ ያሳያል ብለዋል፡፡

የሰላሙ ባለቤት ትግራይ ውስጥ ያለው ህዝባችን በመሆኑ እንተውለት ነው ያሉት በመልዕክታቸው፡፡

“መላው የትግራይ ሕዝብ÷ ባለፉት አመታት ያጋጠሙህን ጉልህ ችግሮች በተለየ ግምገማ ልትፈትሽና ዘላቂ ሰላምህን የሚያረጋግጥ ንቁ ስራ ለመስራት የምትችልበት የተሻለ ተስፋ በደጅህ አለና ንቃ” ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

“በትግራይ ከየትኛውም ሀይል ችሮታና ተነሳሽነትን ሳትጠብቅ፣ ብዝሀ-ሀሳብና አደረጃጀት የሚያመቻች አጋጣሚና ሰፊ መድረክ እንዲፈጠር ይህንን አይነተኛ የሰላም እድል ለመጠቀም በአፋጣኝ ራስህን ለምክክር እንድታዘጋጅ” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

“የሰላምህ ዋና ጠባቂ ራስህ መሆንህን የሚያስመሰክር ብልህ እርምጃ መውሰድ እንድትጀምር” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

መላው የትግራይ ሕዝብ÷ የፌደራል መንግስትና የመከላከያ ሰራዊት አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በቀጣይ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ደግፈህ እንድትቆምና ትብብርና ተሳትፎህንም ሳትቆጥብ እንድትቀጥልበት ጥብቅ የአደራ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ ብለዋል፡፡

“በትግራይ ብሎም በመላው ሀገራችን ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የነበረን ጥሩ አጋጣሚ የተሰጠን በለውጡ ጅማሬ ቀናት የዛሬ አራት አመት ገደማ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ፥ “ሁለተኛው ጥሩ የሰላም እድል ደግሞ አሁን በእጃችን ገብቷልና ሁላችንም በጋራ እንንቃ ብለዋል በመልዕክታቸው።

የሰላም ጭላንጭል አጋጣሚያችንን ከነጣቂዎች እንጠብቅ፤ በስክነትና በምክክር እናጽና በተደራጀ ተግባራችንም እንደግፍ ነው ያሉት ዶክተር አብረሃም።

ባሳለፍነው ችግር ምክንያት የተፈጠረውን ከባድ ስሜት፣ በህዝባችን ማህበረ ስነ-ልቡና ውስጥ ያለመተማመንና መዛል ተስተውሏል ያሉት ዶክተር አብረሃም÷ በዚህ ረገድ የእምነት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጥበቡ ማህበረሰብ እና የማህበረሰብ አንቂዎች ይህን የህዝባችን ሁኔታ ለመመለስ ኃላፊነት በተሞላው መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.