ታዳጊ ሀገራት የዓየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ገፈት ቀማሽ መሆን አልነበረባቸውም – ፓውል አኪውሚ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ታዳጊ ሀገራት ለዓለም አቀፉ የዓየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መንስዔ ባልሆኑበት ሁኔታ የችግሩ ዋና ገፈት ቀማሽ መሆን እንደማይገባቸው ተገለጸ፡፡
ጉዳዩን በንግድ ላይ በሚወጣው ሳምንታዊ የተመድ ትንበያ ያነሱት በድርጅቱ የአፍሪካ እና የታዳጊ ሀገራት የንግድና ልማት ኮንፈረንስ ዳይሬክተር ፓውል አኪውሚ ናቸው፡፡
ጋናዊው ዳይሬክተር ፓውል አኪውሚ ÷ የዓለማችን 46 ታዳጊ ሀገራት ከአንድ ቢሊየን በላይ ሰዎች እንደሚኖርባቸው የገለጹ ሲሆን ለካርበን ልቀት እና ለዓየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ያላቸው አሉታዊ አበርክቶ ግን አንድ በመቶ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
ነገር ግን ታዳጊ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚደርሱ የአውሎ ነፋስ፣ የጎርፍ ፣ የሙቀት መጨመር እና የበርሃማነት መሥፋፋት አደጋዎች ዋና ተጠቂ መሆናቸውን በመረጃቸው ጠቁመዋል፡፡
ያደጉ ሀገራት ለዓለማችን የዓየር ንብረት ለውጥ እና ከአስከፊ የካርበን ልቀት መጠን ጋር ተያይዞ በሰው ልጆች በተለይም በታዳጊ ሀገራት ላይ ለሚከሰቱ የጤና እክሎች እና የዓየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች ተጠያቂ መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡
በመሆኑም ለሚያደርሱት ተፅዕኖ ታዳጊ ሀገራት ፍትሃዊ በሆነ የማካካሻ ፈንድ እና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት መደገፍ እንዳለባቸው አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
27ኛው የ2022 የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ የፊታችን ዕሁድ በግብፅ ሻርም ኤልሸክ ይጀመራል፡፡
ኮንፈረንሱ እስከ ፈረንጆቹ ሕዳር 18 ይቆያልም ነው የተባለው።
በኮንፈረንሱ ታዳጊ ሀገራት ጥቅማቸውን የሚያረጋግጥ ሐሳቦች እንደሚያነሱ እና አንዳንድ አወንታዊ ውሳኔዎች ላይ እንደሚደረስም ይጠበቃል፡፡