የሀገር ውስጥ ዜና

ከ255 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ካናቢስ እና ሌሎች የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ

By Tamrat Bishaw

November 05, 2022

አዲስ አበባ በ፣ ጥቅምት 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን ከ255 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ካናቢስ እና ሌሎች የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ከጥቅምት 18 እስከ 24 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 144 ነጥብ 8 ሚሊየን የገቢ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች እና 195 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር በላይ የወጪ በአጠቃላይ 339 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር የሚያወጡ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዙን አስታውቋል።

በእነዚህ ቀናት ውስጥ 24 ነጥብ 1 እና 8 ነጥብ 2 ኪሎ ግራም የሚመዝን ከ255 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ እፅ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከሀገር ሊወጣ እና ሊገባ ሲል መያዙን ገልጿል።

ከተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ ዕቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እፆች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች እንደሚገኙበት ከጉምሩክ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።