በመንግሥት እና በህወሓት መካከል ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት እንተጋለን – የአፋር ክልል መንግሥት
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ክልል መንግሥት በኢፌዴሪ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት የሚተጋ መሆኑን ገለጸ።
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሰላም ስምምነቱን አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ ሙሉ መልእክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የጋራ ጥቅም ባስከበረ መልኩ የተጠናቀቀው ስምምነት ኢትዮጵያውያንን እና ለሰላም ዘብ ለቆሙ አካላት በሙሉ እጅግ ያስደሰተ እና ስምምነቱ በዋናነት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት እንድነትን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
ለዚህ ስምምነት ተፈፃሚነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ሀገራችንን ወደ ሰላም የመመለስ እና በጦርነቱ ወቅት የደረሰውን የማኅበራዊ ሥነ-ልቦና እና የቁሳዊ ጉዳት ለማስተካከል በጋራ ሆነን የምንሠራ ይሆናል።
ለሁለት ዓመታት በነበረው ጦርነት የሕይወት፣ የሥነ-ልቦና እና የንብረት ኪሳራ ደርሷል።
ከሰላም በፊት የሚቀድም ሌላ ምንም ዓይነት አማራጭ ባለመኖሩ የተደረሰው ስምምነት ላይ የተጠቀሱ ዋና ዋና ነጥቦች ተተግብረው ሀገራችን ወደ ተረጋጋ ሁኔታ ማሻገር እንዲቻል ሁሉም አካል ኃላፊነቱን መወጣት ግድ ስለሚል በጋራ ለተግባራዊነቱ እንተጋለን።
ወደ ቀጣይ ከፍታ ለመሻገር ያለን ዋነኛ አማራጭ ለጋራ ሀገር በጋራ አንድ ሆኖ መጓዝ በመሆኑ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የኅብረተሰባችን ክፍሎች ከጉዳታቸው አገግመው ወደ ቀደመው ማኅበራዊ ትስሥራቸው እንዲመለሱ እጅ እና ጓንት በመሆን እንሠራለን።
የነበረው ግጭት በተለይም የጦርነቱ ቀጠና የነበሩ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ ጉዳትን ያስተናገዱ ሲሆን ጉዳቱ ግን የሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ በግጭቱ የወደሙ ተቋማትን ጨምሮ መልሶ የመገንባት ሥራዎች ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እና የኢትዮጵያ ወዳጅ ሁሉ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
እንደ አፋር ሕዝብ በጦርነቱ የደረሰው ጉዳት እጅግ የከፋ ቢሆንም በጦርነቱ ውስጥም ሆኖ እንደ ሕዝብም እንደ መንግሥትም ለወንድም የትግራይ ሕዝብ ትልቅ ክብርን በመስጠት ሰብአዊ እርዳታ እንዲያገኝ ከማድረግ ጀምሮ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትልቅ ሥራ ተሠርቷል።
ይህን መልካም ሥራም በማስቀጠል ከጎረቤት ሕዝቦች ጋር የሰላም እና የልማት ትብብርን ለማጠናከር የአፋር ክልል ሕዝብ እና መንግሥት ቁርጠኛ ነው።
በጦርነቱ ምክንያት እንደ ሀገር የደረሰብንን የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲና ሌሎች ተያያዥ ጫናዎችን በማስተካከል በኩልም ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል።
ሀገራችን ሉዓላዊነቷን ባከበረ እና ባስጠበቀ መልኩ ከተቀረው ዓለም ያላት ግንኙት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ በርትተን መሥራት ይጠበቅብናል።
በመጨረሻም የሀገራችንን ሰላም በማይሹ አንዳንድ አካላት የሰላም ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚነዙ የውሸት ወሬዎች እና የጥላቻ ንግግሮችን በመከላከል ረገድም አብሮነትን፣ ለሰላም ቅድሚያ መስጠትን ትኩረት በመስጠት ጥረት ልናደርግ ይገባል!
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ጥቅምት 26 -2015
ሰመራ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!