አቶ ደመቀ መኮንን ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላሂ ቢን ዛይድ ጋር ተወያዩ።
በውይይታቸው ወቅትም በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ እና በሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ መክረዋል።
በዚህ ወቅት አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ስለተፈረመው ስምምነት ገለፃ አድርገውላቸዋል።
ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ያረጋገጡት አቶ ደመቀ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ እያደረጉ ላሉ አካላት ምስጋና ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
በተጨማሪም በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር እና ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ በኢትዮጵያ በኩል እየተሰሩ ስላሉ ስራዎች አብራርተዋል።
የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላ ቢን ዛይድ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሃት መካከል በተፈረመው የሰላም ስምምነት የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።
የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ልዩ መሆኑን የገለፁት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግንኙነቱን በሚመጥን ደረጃ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!