Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶጉሉ ጋር በአቡዳቢ ተወያይተዋል፡፡

አቶ ደመቀ በተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች አዘጋጅነት በሚካሄደው የሰር ያሲ ባን ፎረም ጎን ለጎን ነው ከቱርክ አቻቸው ጋር የመከሩት፡፡

በውይይታቸውም በሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

አቶ ደመቀ ባሳለፍነው ሳምንት በፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል ስለተፈረመው የሰላም ስምምነት ለሚኒስትሩ ገለፃ አድርገዋል።

መንግስት በዘላቂነት ሰላምን ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንሚገኝም ነው ያብራሩት፡፡

ኢትዮጵያ እና ቱርክ ዘመንን የተሻገረ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ደመቀ÷ አሁን ላይ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩ ተግባራት በተለያዩ መስኮች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውሰዋል።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶጉሉ በበኩላቸው÷ በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት በውይይት ለመፍታት የሰላም ስምምነት በመፈረሙ የቱርክ መንግስት የተሰማውን ደስታ ገለፀዋል።

የኢትዮጵያ ሰላም ለቀጠናው መረጋጋት ጭምር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመው÷ የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ቱርክ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደምትሰጥ አረጋግጠዋል።

ቱርክ በሁሉም መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መናገራቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.