Fana: At a Speed of Life!

አቶ ኡመድ ኡጁሉ በጋምቤላ አጠቃላይ ሆስፒታል የተገነባውን የኦክስጅን ማምረቻ ማዕከል መረቁ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ርዕሠ-መስተዳድር ኡመድ ኡጁሉ በጋምቤላ አጠቃላይ ሆስፒታል የተገነባውን የኦክስጅን ማምረቻ ማዕከል መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡

በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉን ጨምሮ ሌሎች የክልሉና የፌደራል መንግስት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡

በጋምቤላ ክልል በኦክስጅን እጥረት ምክንያት በርካታ ሕሙማን ለኅልፈተ ሕይወት ሲዳረጉ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

የጋምቤላ አጠቃላይ ሆስፒታል የኦክስጅን ሲሊንደሮችን ለመሙላት አዲስ አበባ ድረስ ለመሄድ ይገደድ እንደነበረና በዓመት እስከ ሁለት ሚሊየን ብር ወጪ ያወጣ እንደነበረም ተመላክቷል፡፡

ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው ማዕከልም በክልሉ ሲያጋጥም የነበረውን የኦክስጅን አቅርቦት እጥረት እንደሚያስቀር እና ለሌሎች አጎራባች ክልሎችም እንደሚተርፍ ተነግሯል፡፡

አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ÷ የኦክስጅን ማምረቻ ማዕከሉ የሚፈለገውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል ከማዕሉ ባለሙያዎች በተጨማሪ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው ÷ የማዕከሉ መገንባት በኦክስጅን እጥረት ይከሰት የነበረውን ኅልፈተ ሕይወት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ ተናግረዋል።

በክልሉ ዘመኑን የዋጀ የሕክምና ተቋም እንዲኖርም ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.