Fana: At a Speed of Life!

ስምምነቱ ዘላቂ ሠላም በማስፈን ሙሉ ትኩረታችንን በልማትላይ ለማዋል ፋይዳው የጎላ ነው – የሶማሌ ክልል

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ስምምነቱ በኢትዮጵያ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሠላም ለማስፈን ብሎም አንድነታችንን በማጠናከር ሙሉ ትኩረታችንን በልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ ላይ ለማዋል ፋይዳው የጎላ ነው ሲል የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ገለጸ፡፡

የሶማሌ ክልል ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ በመንግስት እና ህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ባከበረ መልኩ የተፈጸመ መሆኑን አንስቷል፡፡

የሰላም ስምምነቱ ÷ ሠላም ወዳድ ለሆኑ ወገኖች ሁሉ ከፍተኛ ደስታን የፈጠረ ነው ሲል መግለጫው አውስቷል፡፡

የሶማሌ ክልል ሕዝብ እና መንግስት ከለውጡ በኋላ ባሉት አራት ዓመታት በክልሉ በሰፈነው አስተማማኝ ሰላም ምክንያት የሰላምን ትክክለኛ ዋጋና ጥቅም በተጨባጭ ለመረዳት ችሏልም ነው ያለው።

በመሆኑም ክልሉ የተደረሰው የሠላም ስምምነት በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲሆን በሙሉ ልብ እንደሚደግፍ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም የጦርነት አውድማ በነበሩ አካባቢዎች የደረሰውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት መልሶ ለመጠገን በሚደረገው ማንኛውም ጥረት ሁሉ ክልሉ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ግንባር ቀደም ሆኖ እንደሚሰለፍ ነው ያስታወቀው፡፡

የሶማሌ ክልል ሕዝብና መንግስት እንደ ሀገር ከተረጂነት ለመውጣት እና ብልፅግናን ለማረጋገጥ ለተጀመረው ዘርፈብዙ እንቅስቃሴ ዋነኛው መሰረተ ሠላም መሆኑን ይገነዘባልም ብሏል መግለጫው።

ስምምነት የተደረሰባቸው አንኳር ጉዳዮች በሁሉም ወገኖች ቅቡልነት ባለው መንገድ ተግባራዊ እንዲሆኑና በሀገራችን ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍንም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል።

መግለጫው በጦርነቱና ተያያዥ ምክንያቶች እንደ ሀገር የደረሰው መከራና ስቃይ እንዲሁም የተከፈለው መስዋዕትነት ብዙ ቢሆንም ከሁሉ የሚበልጠውን ሀገራዊ አንድነት በማሰብ በደልን ከመቁጠር ይልቅ በይቅር ባይነት መንፈስ ወደ ነገ አሻግሮ ማየት እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡

በተለይም በጦርነቱ በተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሕዝብ ለሕዝብ ትሥሥሩና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሩ ወደ ቀደመ ቦታው እንዲመለስ ተቀራርቦ በጋራ መስራት ያስፈልጋልም ነው ያለው።

በጦርነቱ ምክንያት የደረሰው ጉዳት በጥቅሉ በሀገር ላይ የደረሰ ጉዳት መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባትም የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ወገኖቻችንን መልሶ ለማቋቋም ፣ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኝ ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ በአንድነት ሊሰለፍና በቀና መንፈስ በመደገፍ በሰቆቃ ውስጥ ላለፉ ወገኖቹ አለኝታነቱን ሊያሳይ እንደሚገባም በመግለጫው ተነስቷል፡፡

የሀገራችንን ሠላምና ብልፅግና በማይሹ ወገኖች በሚሸረብ ሴራ የሠላም ሂደቱ ወደ ኋላ እንዳይቀለበስ ለሚደረገው ጥረት የሶማሌ ክልል ሕዝብና መንግስት የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.